በኢትዮጵያ የከተሞች በዓል ላይ የሃዋሳ ከተማ ተሳትፎ



ከተሞች ተሞክሯቸውን እየተለዋወጡ ናቸው 
ዜና ሐተታ

አዳማ እንግዶቿን ማስተናገድ ከጀመረች ቀናትን አስቆጥራለች። ማዕዷን እያቋደሰች የምትገኘዋ አዳማ ገፅታዋን ለማስተዋወቅ የአራተኛው የከተሞች ሣምንት ኤግዚቢሽን ተሣታፊ ነች።
ለሰባት ተከታታይ ቀናት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ የቆየው ኤግዚቢሽን 136 ያህል ከተሞች ወደ አዳማ ያመጣቸውን መገለጫዎቻቸውን በድንኳን በድንኳን ሆነው ራሳቸውን እያስተዋወቁ ናቸው።
የአዳማና ዙሪያዋ ከተሞች በርካታ ነዋሪዎች ኢግዜቢሽኑን ይጐበኛሉ። ነዋሪዎቹ አዳማ በዘንድሮው የከተሞች ውድድር አንደኛ እንደምትወጣ ይገልፃሉ። የከተማዋን ገፅታ በኤግዚቢሽኑ እያስጎበኙ የሚገኙ አካላትም ይህንኑ ያጠናክራሉ።
አቶ ዘላለም አስራት የአዳማ ከተማን ገፅታ ለማሳየት በተዘጋጀው ድንኳን ውስጥ ስለቀረቡት የተለያዩ ዝግጅቶች ሲያብራሩ «የአዳማ ከተማን ማስተዋወቅ ያስፈለገው ከከተሞች ሁሉ በመሪነት ቦታ ላይ እንድትቀመጥ ታስቦ ነው» ይላሉ።
እንደ አቶ ዘላለም ማብራሪያ፤ የአዳማ ከተማ ከ63 ሺ በላይ አባላትን ያቀፉ ከ4ሺ 73 በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አሏት። ከ280 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዷ በአስፋልትና በኮብልስቶን ተሸፍኗል። ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቀሱ ከ700 በላይ ባለሀብቶች ይገኙባታል።
አዳማ በቀን 45 ሺ የሚሆኑ ሕዝብ ገብቶ የሚወጣበት 7ሺ ያህል ሰዎች ደግሞ የሚያድሩባት ናት። 8ሺና ከዛ በላይ እንግዶችን ሊያስተናግዱ የሚችሉ የተለያዩ የስብሰባ ማዕከላት ያሏት ስትሆን። ይህም ከተማዋን የኮንፈረንስ ከተማ አሰኝቷታል። ለኢንዱስትሪ፣ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ለሪልስቴት፣ ለጤና፣ ለትምህርትና ለተለያዩ ዘርፎች የሚውል 128ነጥብ 70 ሔክታር መሬት ለልማት ማዘጋጀቷንም አቶ ዘላለም ይጠቁማሉ። 
የሀዋሳ ከተማን ወደሚያስተዋውቀው ድንኳን ዘለቅን። «እኛ በአዳማ የተገኘነው ሕብረ ብሔራዊቷንና የደኖች ከተማ የሆነችውን አዋሳን ለማስተዋወቅ ነው» ያሉት የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩ ወልዴ፤ ለማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶች ወደ ከተማዋ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን ሥራ ላይ እንዲያውሉ ለመጋበዝም መሆኑን ነው የሚገልጹት።
የሀዋሳ ከተማን በዘጋቢ ፊልም፣ በቻርት፣ የተለያዩ ሲዲዎችን በማቅረብ እንዲሁም በመቅረፀ ድምፅ የማስተዋወቁ ሥራ ተካሂዷል።
ከሐይቁ ማዶ አዲስ ከተማ ለመመሥረትም እቅድ እንዳለ የተናገሩት አቶ ብሩ፤ የዚህንም መዋቅራዊ ፕላን እያሳዩ ከተማዋን ያስተዋውቃሉ።
የተለያዩ ዘመናዊ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በከተማዋ እንዳሉም ነው የሚገልጹት።
እንደ አቶ ብሩ ገለፃ፤ የሐዋሳ ከተማ መሠረተ ልማት የተሟላላት ናት። ወደ 324ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የአስፓልት፣ የኮብልስቶንና የጠጠር መንገድ አላት። የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋኗም ወደ 75 በመቶ ደርሷል።
የከተማዋ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የሆቴል፣ የኢንዱስትሪ፣ የመኖሪያ ቤቶችና ሌሎች ልማቶችን በማሳያነት ቀርበዋል።
የሀዋሳ ሐይቅ በገንዳ ተመስሎ የቀረበ ሲሆን፤ ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ እንደሆነችም የሚያመላክቱ ማሳያዎች ቀርበዋል። ምንም እንኳን ከተማዋ ባለፈው ዓመት ሦስተኛ ብትወጣም በውጤቱ ደስተኛ እንዳልነበሩ ያስታወሱት አቶ ብሩ፤ ዘንድሮ የማስተዋወቅ ስልቷን ቀይሳ ከተማዋ ከአምናው ይልቅ በርካታ ማሳያዎችን ይዛ መቅረቧን ነው የተናገሩት። ይህም የአንደኝነት ደረጃዋን ለማግኘት እንደሚያስችላት ሙሉ እምነት እንዳለቸው ነው ያመለከቱት።
«'ትንሿ ኢትዮጵያ' አዋሳ ተመራጭ ነች» ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ይህንን ለማለት ያስደፈራቸው ከጎብኚዎቹ ያገኙት መረጃም ጭምር እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
አርባ ምንጮች አዞና አሳ ከነህይወታቸው ይዘው በኤግዚቢሽኑ ላይ ቀርበዋል። ዓሳ ልክ ከአባያ ወይም ከጫሞ ወጥቶ እንደሚፈራገጥ አይነት ከሰሩት ከገንዳ በማውጣት እየጠበሱ ታዳሚዎቻቸውን ያቀምሳሉ።
የአርባ ምንጭ የነጋዴ ሴቶች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ አለም አሉላና የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሠራተኛ አቶ ዘውዴ ገረሱ ከተማዋ አንደኛ እንድትወጣ የሚያስችላትንና እንታወቅበታለን ያሉትን ሁሉ ይዘው በኢግዚቢሽኑ ላይ መገኘታቸውን ይገልጻሉ።
በምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የምትገኘው አርባ ምንጭ በአባያና በጫሞ ሀይቅ አጠገብ እንደምትገኝ ይናገራሉ። አቅራቢያዋ ያለው የነጭ ሣር ፓርክም ብርቅዬና ድንቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፍ አቅፎ ይዟል። እነዚህም የብዙ ቱሪስቶች መዳረሻ እንድትሆን እንዳስቻላት ነው የገለጹት።
እድሜ ጠገብ ከሆኑ ደኖቿና ከአርባ በላይ ምንጮቿ የሚፈልቀው ውሃም ለውበቷ ትልቁን ድርሻ እንደሚያበረክትላትና ለጎብኚዎቿ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ሪዞርቶች እንዳሉም ያመለክታሉ።
ከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየሠራን ነው ሲሉ ጠቁመው፤ ትኩረት የተደረገው በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ላይ መሆኑን ያብራራሉ። ለዚህም በርካታ የከተማዋ ወጣቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን ጠቁመው፤ በተለይም ሴቶች በማህበር ተደራጅተው የሚያመርቷቸውን የባህል አልባሳት ይጠቅሳሉ።
የነገሌ ቦረና ከተማ በኤግዝቢሽኑ ከተሳተፉት አንዷ ናት፤ ከተማዋ በኤግዚቢሽኑ ይዛ ስለቀረበችው ያብራሩት አቶ ደያን አብዱ፤ «ከተማዋ ውሃ ለጠማው ወተት የምታቀርብ ናት» ይላሉ። እርጎ በጮጮ ለማሳያነት አስቀምጠዋል።
በከተማዋ መሰረተ ልማት እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረው፤ በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድና በሌሎችም የተሻሉ ለውጦች አሉ ይላሉ።
ነገሌ ቦረና ተፈጥሮ ያደላት ምቹ ሀገር መሆኗን የሚናገሩት አቶ ደያን፤ ለኮብል ስቶን ያለምንም ልፋት አገልግሎት ላይ ሊውል የሚችል ድንጋይ ሀብት ያላት መሆኑን ይገልጻሉ። ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚሆነው አሸዋ እንዳላትና በቀላሉ ወደ ሥራ ለመግባት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑንም ይናገራሉ። 
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=headline&newsId=10111

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር