‹‹ሐዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ……


በሔኖክ ረታ
ኅዳር መባቻ ማለዳ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰበሰበው የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ሴንተር (ኤምሲሲ) ሠራተኛ በድርጅቱ አማካይነት የተሰናዳለትን የሽርሽር ጉዞ ለመጀመር በንቃት ቦታ ቦታውን ይዟል፡፡ ሁለተኛውን የሚዲያና የኪነጥበብ ባለሞያዎች የእግር ኳስ የዋንጫ ውድድርን በሦስተኛነት በማጠናቀቁ ነበር ከሌሎቹ አሸናፊዎች ጋር በመሆን ይህን የጉዞ ዕድል ያገኘው፡፡

ከማለዳው አንድ ሰዓት ላይ ወደ ሐዋሳ ከተማ የተጀመረው ጉዞ ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ዱከም ከተማ ላይ የቁርስ ቆይታ ነበረው፡፡ በቀድሞው አትሌት ወርቁ ቢቂላ ሆቴል ቁርስ የተመገቡት የኤምሲሲ አባላት ከቀድሞው አትሌት ጋር ትውውቅና የተወሰነ ቆይታ የማድረግ አጋጣሚም ነበራቸው፡፡ ቢሾፍቱንና ሞጆን በተከታታይ አልፎ በግምት አምስት ሰዓት ገደማ ላይ የካስቴል ወይን እርሻና ፋብሪካ ለመጎብኘት አዳሚ ቱሉ ወረዳ ደርሷል፡፡ በዘመናዊ ማሽኖችና ቴክኖሎጂዎች የተገነባው የወይን መጥመቂያ ፋብሪካ ከተንጣለለው የወይን እርሻ በሰው ኃይል አማካይነት የተለቀመውን ፍሬ በረዥም የጊዜ ሒደት ውስጥ የሚፈለገውን የወይን ጣዕም አቀነባብሮ ለገበያ የሚያቀርብ ግዙፍ የወይን እርሻና ማምረቻ እንደሆነ በድርጅቱ የምርት ክፍል ባለሞያ የሆኑት አቶ ዳዊት ገብሬ ለጎብኚዎቹ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ እንደ ብረት ምጣድ በጋለው የመኪናው ጣራና ግድግዳ በኩል እየገባ የሚፋጀው ጠራራ ፀሐይ ጎብኚዎችን በከፍተኛ ሙቀት ቢፈትንም በጨዋታና በሙዚቃ የተዋዛውን ጉዞ ሊያደበዝዘው አልቻለም ነበር፡፡

መቂ፣ ዝዋይንና አርሲ ነገሌ ከተሞችን በፈታኝ የፀሐይ ሙቀት የጨረሰው ጉዞ ሰባት ሰዓት ገደማ ላይ ከመዳረሻዋ የሐዋሳ ከተማ በ23 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ብቻ ቀደም ብላ የምትገኘውን ሞቅ ያለችውን የሻሸመኔ ከተማን ደርሷል፡፡ ሻሸመኔ እንደ ታዋቂ ስሟና የንግድ ማዕከልነቷ በዕድገቷ የምትታወቅ አይደለችም፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ የደቡብ ኢትዮጵያዋን ሙሽራ ክንብንቧን ገልጠን እናያት ዘንድ በሩን ከፍታ ያስገባችን የጥቁር ውኃ መንደርም የምዕራብ አርሲ ዞኗ ዋና ከተማ የሆነችው የሻሸመኔ ወረዳ ክፍል ናት፡፡ በከተማዋ መግቢያ ጫፍ ላይ የተወሰነ አካሉን አጋልጦ የተኛው የሐዋሳ ሐይቅ የከተማዋ የውበት ፈርጥ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከተሞች ልማት መርሐ ግብር ከፍተኛ የዕድገት እመርታን ያሳየችው ሐዋሳ ከዘመናዊ ሕንፃዎቿና አዳዲስ መንገዶቿ በላይ በጥንቃቄ የተነደፈው ፕላኗ ለውበቷ ከፍተኛ አስተዋፆኦ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ የተቆረቆረችበትን ሃምሳኛ ዓመት በቅርቡ ያከበረችው የሐዋሳ ከተማ ተፈጥሮ የቸረቻትን መልካ ምድራዊ ገጽታ ከዘመናዊው የከተማነት ሥልጣኔ ጋር አጣምራ በከፍተኛ የዕድገት ጉዞ ላይ እንደምትገኝና ከአገራችንም አልፎ በአፍሪካ ተመራጭ የመዝናኛና የመኖሪያ ከተማ የምትሆንበትን ዘለግ ያለ ጉዞ ከወዲሁ የተያያዘች መሆኗን በእርግጥም መመስከር ይቻላል፡፡

በከተማዋ ከሚገኙ ምቹ ሆቴሎችና ማረፊያዎች መካከል አንዱ በሆነውና በከተማዋ ዳር በሚገኘው ጨምበላላ ሆቴል የመኝታ ርክክብና ምሳ ያደረገው የኤም.ሲ.ሲ ቡድን በከተማዋ መውጫ ላይ በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን የቢጂአይ የደቡብ ቀጣና ምርት ማምረቻና ማከፋፈያ ፋብሪካንም ጎብኝቷል፡፡

ከብቅል ማበጠሪያውና መፍጫው ጀምሮ እስከ መጨረሻው የቢራ ምርት ድረስ ያለውን ረዥም የምርት ሒደት በተቀላጠፈ ሁኔታ ሲያስረዳ የነበረው የፋብሪካው የምርት ቁጥጥር ባለሞያ አቶ ሱራፌል ቦጋለ ፋብሪካው በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የምርት ፍላጎት ለማማላት በሰፊው እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አክሎ ገልጿል፡፡

ከነበረው ረዥም ጉዞና ድካም ጋር ተዳምሮ በቢራ ፋብሪካው የተገኘው የጎብኚዎች ቡድን በቢራ ፋብሪካው የተመለከተው የምርት ሒደት አስደስቶታል፡፡ በፋብሪካው የመዝናኛ ክበብ (ቢር ጋርደን) ውስጥም ዘና ብለዋል፡፡ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት በዘለቀው ፕሮግራም ላይ ጎብኚዎች እርስ በርሳቸው ከመጨዋወትና ከመዝናናት ባሻገር የፋብሪካው ኃላፊዎች ያዘጋጁትን ስጦታ ለጎብኚዎች በማበርከትና በተለይ ደግሞ ቢራ ፋብሪካው ከስፖርት ጋር በተያያዘ ለውድድሮች መሳካት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል የገባበት አጋጣሚ ለማድመጥ አስችሏል፡፡ በዚህ መልኩ መታደስ የጀመረው የጎብኚዎቹ መንፈስ ቀጥሎ በፖስት ራንዲቩ ሬስቱራንት የራት ፕሮግራም አድርጎ በካምፋየር (የምሽት እሳት) የታጀበ የመዝናኛ ዝግጅት ደማቁን ምሽት አሳርጓል፡፡ በማግስቱ ጠዋት የቁርስ ቆይታውን በሌዊ ሆቴል ያደረገው የኤምሲሲ (ሪፖርተር) ቡድን በከተማዋ የሚገኘውንና አሞራ ገደል የተሰኘውን የመናፈሻ ስፍራ ጎብኝቶ ረፋዱ ላይ ወደ አዲስ አበባ የሚመልሰውን ጉዞ ጀምሯል፡፡ በመልሱ ጉዞ አብዛኛው ጎብኚ የተደሰተበትን ነገር እያነሣ ሲስቅና ሲዝናና የነበረ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ ያለቅጥ የተንሰራፋውን የዘመናዊነት አባዜ ይህንንም ተከትሎ በየመዝናኛ ሥፍራው በተለይ በምሽት የሚስተዋለው ዋልጌነት የከተማዋን ነዋሪ በተለይም ታዳጊ ሕጻናትን ከመንገዳቸው እያቋረጠ በእንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሕይወት ውስጥ ከቶ እንዳያስቀራቸው በመስጋት ጭምር ሲያወያይም ነበር፡፡

የሐዋሳን ተፈጥሮኣዊ ውበት የከተማው አስተዳደርንና ነዋሪዎች ከዘመናዊነት ጋር በጥሩ ጥበብ እንዳሳመሩት ሁሉ የከተማዋን ደኅንነትና ኢትዮጵያዊነትንም በወጉ ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባም ከማሳሰብ አልተቆጠበም፡፡ የጎብኚዎች ቡድን እሑድ አመሻሹ ላይ ነበር ወደ አዲስ አበባ የድምፃዊ መልካሙ ተበጀን “ሐዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሔጄ ያየኋት ያች የሲዳሞ ቆንጆ……” ዜማ እያለ የከተማዋን ውበት እያሞጋገሰና ደግሞ ተመልሶ የሚጎበኝበትን ቀን እየናፈቀ የደረሰው፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/300-social/8539-2012-11-17-11-16-36.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር