ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ከተሞች የህዳሴ ጉዞ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንደሚገኝ ገለፁ



“ከተሞች የኢንዱስትሪያሊስቶች መፍለቂያ ማዕከል በመሆን የመለስን ራዕይ ያሳካሉ” በሚል መርህ በአዳማ ሲካሄድ የቆየው 4ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ሳምንት ተጠናቋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በዓሉ በከተሞች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል እና ጠንካሮችን በማበረታታት በዘርፉ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ንቅናቄ መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የከተሞች የህዳሴ ጉዞ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ደመቀ በማደግ ላዩ ያሉ ከተሞችን ወደ ላቀ የልማት ደረጃ ለማሸጋገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በገጠር እየተመዘገበ ያለው የልማት ውጤት በከተሞች እየታየ ላለው መጠነ ሰፊ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡ ከተሞችንና ገጠሮችን አስተሳስሮ መሄድ ቀጣይ የመንግስት አቅጣጫ መሆኑንም ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት፡፡
በ4ኛው የከተሞች ሳምንት ለሰባት ቀናት በቆየው ኤግዚቢሽን ላይ በተለያዩ የከተማ ልማት መስኮች ያከናወኗቸውን ተግባራት እና እራሳቸውን በማስተዋወቅ ከየምድባቸው ላቅ ያለ አፈፃፃም ያስመዘገቡ ከተሞች ተሸልመዋል፡፡
በተለይም በስድስት ቁልፍ የከተማ ልማት ስራዎች የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም በ4ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ሳምንት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስራዎች የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የትግራይ ክልል ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ስራዎች ደግሞ የትግራይ ክልል አንደኛ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አሸናፊ ሆነዋል፡፡
በመኖሪያ ቤቶች ልማትና በመንግስት ኮንስትራክሽን ስራዎች የትግራይ ክልል፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የላቀ አፈፃፀም በማሳየት ተሸልመዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና ሬጉላቶሪ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ትግራይ ክልል እና አዲስ አበባ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በከተማ ፕላን ፅዳትና ውበት ስራዎች ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአንደኝነቱን ደረጃ በመያዝ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በአጠቃላይ በስድስቱም የከተማ ቁልፍ ተግባራት አንድ ላይ ተደምረው ደቡብ ክልል 3ኛ፣ አዲስ አበባ 2ኛ፣ ትግራይ ክልል1ኛ በመሆን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያዘጋጀላቸውን የመኪና ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እጅ ተቀብለዋል፡፡
ልዩ ድጋፍ ከሚሹ አምስቱ ክልሎች መካከል የሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ሶማሌ ክልል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በከተሞች ልማት ዘርፍ የእድገትና ትራንስፎረሜሽን እቅዱ አፈፃፀም እየተሳካ ነው ብለዋል፡፡
በያዝነው አመት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የጀመርናቸውን ስራዎች አጠናክሮ በመስራት ከ1.7 ሚሊዮን በላይ የስራ እድል እንፈጥራለን ያሉት አቶ መኩሪያ ኢንተርፕራይዞቹን ለመደገፍም 3.6 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት መጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ደግሞ የከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመንና በማሻሻል በዘርፉ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን መፍታት ነው ብለዋል አቶ መኩሪያ፤”በአዲስ አበባ ተጀመረው የዘመናዊ የመሬት መረጃ ስርዓት አያያዝ ወደ ክልሎችም እንዲስፋፋ ይደረጋል፡፡”
እንደ አቶ መኩሪያ ገለፃ በከተሞች የቤት ችግርን ለመቅረፍ የ10/90፣ 20/80፣ 40/60 የመሳሰሉ የቤት ልማት ፕሮግራሞች በቅርቡ የሚጀመሩ ከመሆናቸውም ባሻገር አስቀድሞ የተጀመረው የጋራ መኖረያ ቤቶች ግንባታም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በከተማ ፅዳትና ውበት ረገድ በሩዋንዳ የኪጋሊ፣ በአዲስ አበባ የጉለሌ ክፍለ ከተማ በቢሾፍቱ የአብነት መንደር ተሞክሮዎች ተቀምረው ወደ ሌሎች ክልሎችም እንዲሸጋገሩ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
http://www.ertagov.com/amerta/erta-news-archive/48-erta-tv-today-top-news-addis-ababa-ethiopia/2510-2012-11-17-10-08-53.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር