በሀዋሳ ከተማ ከ210 ሚልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የልማት ስራዎች እየተካሄዱ ናቸዉ -በከተሞች ሳምንት ላይ ለተሳተፉ የምስክር ወረቀት ተሰጠ


አዋሳ ህዳር 21/2005 በሀዋሳ ከተማ ከ210 ሚልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ግንባታ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የከተማው አስተዳደር ገለጸ፡፡ በአራተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ላስመዘገበችው አመርቂ ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት፣ ድርጅቶች፣ ማህበራትና ግለሰቦች ትናንት ምሽት የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የከተማው ከንቲባ አቶ ዮናስ ዮሴፍ በዚሁ የምስጋና ፕሮግራም ላይ እንደተናገሩት ከተማዋን ለነዋሪው ምቹ፣ የኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በርካታ የልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸዉ ። ሀዋሳ ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ፣ በሀገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ገጽታዋ የጎላ እንዲሆን የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከልነቷን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል ። በከተማ አስተዳደር፣ በማዘጋጃ ቤት የውስጥ ገቢ፣ በመንግስት መደበኛ በጀትና ከአጋር ድርጅቶች በተመደበው 210 ሚልዮን ብር ወጪ እየተካሄዱ ያሉት 10 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ፣ ከ45 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ የጠጠርና የኮብል ስቶን ንጣፍ ናቸዉ ። በተጨማሪ የባህል ማዕከል፣ ዘመናዊ የመንገድ ላይ መብራትና የውሃ መስመር ዝርጋታዎች፣ እንዲሁም ዘመናዊ ቄራ ግንባታ በዋናነት እንደሚገኙበት አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡ ከመሰረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ እስከ አሁን አብዛኛዎቹ ከ50 በመቶ በላይ መከናወናቸዉንና በጀት ዓመቱ ከፍፃሜ ለማድረስ ጥረት ከወዲሁ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ታገሰ ጫፎ ለተቋማቱ፣ ድርጅቶችና ማህበራት ሰርተፍኬት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት በአመራሩና ከተማ ነዋሪዎች የጋራ ጥረት የተመዘገበ ውጤት በመሆኑ ከተማዋ ከሀገር አቀፍ አልፎ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል፡፡ አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተነደፉ እቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ ራእያቸዉን በማሳካት የድርሻቸዉን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል ።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3664&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር