በሀዋሳ ከተማ ከ113 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ግብር ተሰበሰበ


አዋሳ ጥቅምት 24/2005 በሀዋሳ ከተማ ባለፉት ሶስት ወራት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ከ113 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገቢ በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ ማከናወኑን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ገለጸ፡፡ ከከተማው የሚሰበሰበው ገቢ አጠቃላይ ወጪን በሚሸፈንበት ደረጃ ላይ መድረሱም ተመልከቷል፡፡ የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቃዱ ፍሰሃ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የተሰበሰበው ገቢ ቀጥታና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ ከማዘጋጃ ቤትና ሌሎች የግብር ዘርፎች ነው፡፡ ገቢው ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር በ13 ነጥብ 5 ሚልዮን ብርና ከዓምናው ተመሳሳይ ጊዜም እጥፍ ያህል ብልጫ እንዳለው ገልጸው ከተሰበሰበው ገቢ የተጨማሪ እሴት ታክስ 54 ነጥብ 5 ሚልዮን ብር እንደሚገኝበት አስታውቀዋል፡፡ ብልጫ ያለው ገቢ የተሰበሰበው ከዚህ በፊት በአስፈፃሚ ሰራተኞችና አመራሩ ላይ የሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በዲሲፕሊን እርምጃ ስርዓት እንዲይዝና ለግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ሁሉም ግዴታውን እንዲወጣ ጠንካራ የአሰራር አደረጃጀት በመዘርጋቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በከተማው በተለያየደረጃ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ቁጥር ከ10ሺህ 800 በላይ መድረሱን ጠቁመው በግብር ከፋዩ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በአግባቡ የሚስተናገዱበት ግልፅ አሰራር መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ሰፊ የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚካሄድበትና ከዚህ የሚመነጨው የገቢ አቅም ከኪራይ ሰብሳቢነት በፀዳ አሰራር አሟጦ ለመጠቀም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ገቢው በየዓመቱ ጨምሮ ባለፈው ዓመት ብቻ 250 ሚልዮን ብር መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ መደበኛና ካፒታልን ጨምሮ 220 ሚልዮን ብር ወጪ በመሸፈን የተረፈው ለመንግስት ፈሰስ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮ በጀት ዓመት 430 ሚልዮን ብር በመሳባሰብ አጠቃላይ የከተማውን የሰራተኛ ደመወዝ፣ስራ ማስኬጃ ፣ለልማት የሚውል የካፒታል ወጪ ሙሉ በሙሉ የመሸፈን ፍላጎትን ለማሟላት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3108

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር