በደቡብ ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ትኩረት ተሰጥቷል



አዋሳ፡- በደቡብ ክልል የተደራጀ የትምህርት ሠራዊት በመገንባት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳካት ትኩረት እንደተሰጠው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ትናንት በአዋሳ ከተማ ሲዳማ ባህል አዳራሽ የተጀመረውን የክልሉን 18ኛ የአጠቃላይ ትምህርት ጉባዔ በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት፤ በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ የተደራጀ የትምህርት ሠራዊት በመገንባት ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት በትኩረት ይሰራል።
የትምህርት ሥርዓቱ ብቃት ያለውና የተደራጀ ባለሙያ የሚያፈራ መሆን እንዳለበት የገለጹት አቶ ሽፈራው፤ የትምህርት ጥራት ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው ለራሳቸው እና ለሀገራቸው በሚያበረክቱት አስተዋፅኦ እንደሚለካ ተናግረዋል። የትምህርት ጥራት ተጠብቆ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል አመራሩ የትምህርት ሥራውን በባለቤትነት መምራት እንዳለበት አሳስበዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለፃ፤ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሠራዊት ግንባታ እንዲካሄድ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል። በ2004 ዓ.ም በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች በተማሪው ውጤት ላይ በተወሰነ ደረጃ መሻሻል ታይቷል። በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች የተማሪዎችን ውጤት አሁን ካለበት ደረጃ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል።
ሕፃናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በአካባቢያቸው እንዲያገኙ ለማድረግ በ2004 ዓ.ም የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ በሚገኙ 958 ቀበሌዎች እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸውን አቶ ሽፈራው አስረድተዋል።
ትምህርት ቤቶች ያልተከፈቱባቸው ቀበሌዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ በተያዘው የበጀት ዓመት ሁሉም የክልሉ ቀበሌዎች እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች እንዲኖራቸው አመራሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል። ወላጆች በትምህርት ሥራው ተሣታፊ እንዲሆኑ እነርሱንም አደራጅቶ ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሁሉም ሠርተፍኬት ያላቸውን የአንደኛ ደረጃ መምህራን ዘንድሮ ወደ ዲፕሎማ ፕሮግራም እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል። በትምህርት ዘመኑም የሚያስፈልጉ መፃሕፍትም በበቂ መጠን ታትመው እየተሠራጩ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም በበኩላቸው እንዳሉት፤ ላለፉት 20 ዓመታት በትምህርት ዘርፍ በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤት ተገኝቷል።
ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓትና ለልማት ከሚፈለገው የሰው ኃይል ግንባታ አንፃር አሁንም በትምህርት ዘርፍ ትኩረት ሰጥተው ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት መኖራቸውን አቶ ፉአድ ገልጸው፤ በትምህርት ጥራት ላይ አበረታች ለውጥ ቢታይም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ በአገራችን የአንደኛ ደረጃ አጠቃላይ የትምህርት ተሣትፎ 95 ነጥብ 4 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ትምህርት ቤት ያልገቡበት ሁኔታ ይታያል። እነዚህን ሕፃናት ወደ ትምህርት ገበታ ማምጣት ይገባል።
በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተሣትፎና በልዩ ፍላጐት ትምህርት ላይ ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ፉአድ በትምህርት ሥራ ጠንካራ አመራር በመዘርጋት የቀድሞው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የትምህርት ጥራት የማረጋገጥ ዓላማ እውን ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የደቡብ ክልል የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐ መድ አህመዲን በበኩላቸው እንዳሉት፤ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል። ባለፉት ዓመታት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ በአማካይ በ6 ነጥብ 7 በመቶ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 10 ነጥብ 4 ከመቶ አድገዋል። ከዓመታት በፊት ከግማሽ ሚሊዮን የማይበልጥ የነበረው የክልሉ ተማሪዎች ቁጥር በ2004 ዓ.ም ከ4 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።
በክልሉ የትምህርት ልማት ሠራዊት ግንባታ ሥራ መጀመሩን ያመለከቱት አቶ መሐመድ፤ በአንድ ለ አምስት የተማሪ አደረጃጀት አበረታች እንቅስቃሴ መደረጉን ነው የገለጹት። ወላጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በትምህርት ሥራው የድርሻቸውን መወጣት መጀመራቸውን አመልክተዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባዔ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የክልሉ የካቢኔ አባላት የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የትምህርት አመራር አባላትና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል። በጉባዔው የ2004 ዓ.ም የሥራ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ በ2005 ዓ.ም ጥራቱ የተረጋገጠ ትምህርት ለሕብረተሰቡ ለማድረስ የሚያስችል የዕቅድ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ታውቋል። 
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=headline&newsId=9653

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር