በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ዓለም አቀፍ የጉዲፈቻ አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ



ሃዋሳ፡- በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና አማራጭ የሌላቸውን ሕፃናት በሀገሮች መካከል በሚደረግ የጉዲፈቻ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር እየሠራ መሆኑን ገለጸ።
በሀገሮች መካከል የሚደረገውን የጉዲፈቻ አገልግሎት ለማስፈፀም በወጣው የሄግ ስምምነት የአፈፃፀም ሂደት ላይ የባለድርሻ አካላትን አቅም ለማጎልበት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ላይ የሚኒስቴሩ የሕፃናት መብትና ደህንነት የማስጠበቅ ዳይሬክተር ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁኔ እንደተናገሩት፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና አማራጭ የሌላቸው ሕፃናት በሀገሮች መካከል በሚደረግ የጉዲፈቻ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።
በሀገሮች መካከል የሚደረግን የጉዲፈቻ አገልግሎት ለማስፈፀም በወጣው የሄግ ስምምነት ሰነድ ላይ የተቀመጡ ሕጎችና አሠራሮችን እንዲሁም ኮንቬንሽኑን ለማስተግበር መዘጋጀቱን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ በማዕከላዊ ደረጃ በሚዋቀረው ተቋምና በአሠራሮቹ ዙሪያ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማስፋት መድረኩ ምቹ መሠረት እንደሚጥል ተናግረዋል።
ኮንቬንሽኑን ተግባራዊ ለማድረግ የመንግሥት አካላት ከልማት አጋሮች ጋር በተቀናጀ በበቂ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል።
ሕፃናት በሁሉም ረገድ የሚገጥማቸውን ችግሮች በተቀናጀ መልኩ ለመፍታትና ሁለንተናዊ መብታቸውንና ደህነነታቸውን በተጨባጭ ለማስከበር የሚደረገውን ሀገራዊ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገር አኳያ መድረኩ በተሻለ አቅም እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ውይይቱ በፌዴራልና በክልል የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን ከማጠናከር አኳያ ፋይዳው ጉልህና ውጤታማ እንደሆነም አብራርተዋል።
በሕፃናት ሰብአዊ መብት መጠበቅ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ስምምነቶች ከሀገሪቱ ሕጎችና ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እየተቃኙ እንዲጣጣሙና እውቅና እንዲያገኙ ማስቻል የሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለሕፃናት ሁለንተናዊ መብት መከበርና ማኅበራዊ ድህንነት ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሰነዶች ተቀብላ ማፅደቋ ይታወቃል።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የገቡ ሕፃናት ሲባል ሁለቱንም ወላጆቻቸው ያጡ የአካል ጉዳት ያለባቸው ኤች አይ ቪ/ኤድስ በደማቸው ውስጥ የሚኖርባቸውና ከቅርብ ዘመድ ጋር ተጠግተው ለመኖር ያልቻሉትን እንደሚያካትት ጠቁመዋል። 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር