መንግሥት ኢሕአዴግንና የንግዱን ኅብረተሰብ ያጣመረ የንግድ የልማት ሠራዊት ሊፈጥር ነው


በዳዊት ታዬ
የንግድ ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትን አገራዊ አስተዋጽኦ እንዲወጣ ለማድረግ መንግሥት፣ ኢሕአዴግራና የንግዱን ኅብረተሰብ ያጣመረ የንግድ ልማት ሠራዊት መፍጠር የግድ ነው ሲሉ የንግድ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ይህንን የገለጹት ትናንት በተካሄደው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ በሦስቱ ጥምረት ይመሠረታል የተባለው የንግድ የልማት ሠራዊት አገሪቱ ለጀመረችውና ተግባራዊ በማድረግ ላይ ላለችው ዕቅድ መሳካት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል በማለት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የንግድ የልማት ሠራዊት መፍጠርን በተመለከተ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ በሌሎች ዘርፎች እየተፈጠሩ እንዳሉት የልማት ሠራዊቶች ዓይነት አደረጃጀት እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ ልማታዊ አስተሳሰብ እንዲኖር ሚኒስቴሩ የንግድ አሠራር ለውጥ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ከበደ፣ የንግድ ኅብረተሰቡን ከሚመለከቱ ሁለት ፓኬጆች ጐን ለጐን የንግድ ልማት ሠራዊት ለመፍጠር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

‹‹በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኅን እንደምትሰሙት በሦስት አካላት የሚመሠረት ነው፤›› ያሉት የልማት ሠራዊት ጥምረት የሚፈጠረው ‹‹ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ ከመንግሥትና ከሚመለከተው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹በዚህ ጥምረት መንግሥትን የሚወክለው ንግድ ሚኒስቴር ነው፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር አንፃር ሊፈጠር የታሰበው የንግድ ልማት ሠራዊት መንግሥት፣ ኢሕአዴግንና የንግድ ምክር ቤቶችን በጋራ እንዲሠሩ ዕድል ይፈጥራል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይህም በመግባባትና በመመካከር የሚፈለገውን ወጤት ለማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን ማጠቃለያ የንግዱ ዘርፍ 10.47 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማስገኘት የሚጠበቅበት መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ በሌላ በኩል ግን በንግድ ዘርፉ ላይ ትልቅ ፈተና ተደቅኗል ብለዋል፡፡

ይህም በንግድ ዘርፉ የሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ድርጊት ፈጣን ልማትና መልካም አስተዳደር በማስፈን ጉዞ ላይ ችግር ፈጥሯል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹በተለይ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ ዋነኛ ትኩረት የሚሰጠው የጋራ ጉዳያችን ነው፤›› በማለት፣ ይህንን የጋራ ጉዳይ በጋራ መሥራትና ለሚፈለገው ግብ የንግዱ ኅብረተሰብ አስተጽዋኦ ማድረግ እንዲችል ከተፈለገ፣ ሦስቱ የልማት ኃይሎች የሚፈጥሩት ጥምረት ቁልፍ ተግባር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ይዘጋጃሉ የተባሉት ሁለቱ ፓኬጆች የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን፣ አንዱ የንግድ አሠራርና ውድድር ማጠናከርያ ፓኬጅ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የንግዱ ኅብረተሰብ ፓኬጅ የሚል መጠርያ ያለው መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የተለያዩ የንግድ ምክር ቤች ኃላፊዎች ይፈጠራል ስለተባለው የንግድ ልማት ሠራዊት አደረጃጀት በወሬ ደረጃ ከመስማታቸው ውጭ ዝርዝር መረጃ የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ውይይት የሚደረግበት መሆኑን መገንዘብ መቻላቸውን ተናግረው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8306-2012-10-31-07-16-26.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር