የሲዳማ የፖለቲካ ፓርቲዎች


ከታዛቢው
  • ሲኣን በሲዳማ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት ያለፈ ስራ ስሰራ ኣይታይም
  • የሲዳማ ዲያስፖራ የፖለቲካ ድርጅቶች የኢንተርኔት ላይ ኣንበሶች ናቸው

ይሄ ቀጥዬ የማቀረበው ኣስተያየት የእኔ የግሌ ኣስተያየት ነው። ምናልባት በእኔ ማንነት ላይ ጥርጣሬ ቢኖር እኔ የመንግስት ደጋፊ ወይም ተቃዋሚም ኣይደለሁ፤ እንዲሁም የተቃዋሚዎች ደጋፊም ሆነ የተቃዋሚዎች ተቃዋሚም ኣይደለሁ። እኔ የሲዳም ህዝብ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መብቶች ስከበሩ ማየት የምሻ የሲዳማ ህዝብ ተቆርቋር ነኝ። እባካችሁ ከዚህ ባለፈ ሌላ ስም ኣትለጥፉብኝ ኣደራ።

ስለ እራሴ ይህንን ያህል ካልኩ ወደ ጉዳዬ ልለፍ፦ በተለይ ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ ሲዳማ በፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ ናት ማለት ይቻላል። በተለይ ከክልል ጥያቄ እና ከሃዋሳ ከተማ የወደፊት እጣ ፋንታ በምወሰኑ ጉዳዮች ላይ ህዝቡ ከመንግስት ጋር ተፋጦ መክረሙ ይታወሳል። ታዲያ ይህ ፍጥጫ ከፍጥጫነት ኣልፎ ወይም ኣፍትልኮ የወጣበትም ኣጋጣም ተከስቶ ነበረ በተለይ በወረዳዎች ኣከባቢ። የሆነ ሆኖ ዛሬ ግን ፍጥጫው እየረገበ ያለ ይመስላል።

ይህንን ያነሳሁት ያለፈ ታሪክ ልተርክላችሁ ብዬ ኣይደለም፤ ያነሳሁበት ዋናው ምክንያት ስለ ሲዳማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የታዘብኩትን ጀባ ልላችሁ ብየ ነው። ምን ታዘብክ ብላችሁ ጠይቁኝ ታዲያ! ኣዎን የሲዳማ የፖለቲካ ድርጅቶችን ብዙ እየታዘብኩ ነው። ለመሆኑ የሲዳማ የፖለቲካ ፓርቲዎች እነማናቸው? ይመስለኛል ስለ ፓርቲዎቹ ማውራታችን ካልቀረ ስለ ማንነታቸው በስሱ ማንሳቱ የግድ ይመስለኛል።

እኔ ከልጅነተ ጀምሮ የማውቀው ኣንዳንዴ ስለው ተቃዋሚ ስለው ደግሞ የመንግስት ደጋፊ እየሆነ ሁለት መልክ የሚይዘው የሲዳማ ኣርነት ንቅናቄ(ሲኣን) ከቀድሞው ሲህዴድ ከኣሁኑ ደኢህዴን ቀጥሎ ዋናው የሲዳማ ፖለቲካ ድርጅት ሲሆን ሌሎች ደግሞ፤ በቅርቡ ህብረት የፈጠሩት(እነማን ህብረት እንደፈጠሩ ባይታወቅም) የሲዳማ ፓርቲዎች ቅንጅት ለዲሞክራሲ እና ለፍትህ፤ የሲዳማ ኣርነት ግንባር ወዘተ የተባሉ የዲያስፖራ ተቃዋሚ ድርጅቶች ኣሉ ስባል ሰማለሁ።

ስባል እሰማለሁ ያልኩበት ምክንያት እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች በሲዳማ ምድር ቢሮ ኖሯቸው ኣባላት ኣፍርተው የተደራጁ ባለመሆናቸው ላቃቸው ኣልቻልኩም። እርግጠኛ ነኝ ኣብዛኛው እንታገልለታለን የምሉት ህዝብም በቅጡ የምያውቃቸው ኣይመስለኝም። እንደ እኔ ከሆነ ለህዝቡ ለመታገል ቆርጠው የተነሱ ኣይመስለኝም፤ የምር ለህዝቡ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ብሎም ማህበራዊ መብቶች መከበር የምታገሉ ከሆነ መታገል ያለባቸው ከህዝቡ መካከል ሆነው ነው ብዬ ኣምናለሁ።

ለነገሩ የዛሬ ሃያ ኣመት ኣከባቢ ማለትም ኢህኣዴግ ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ዳግመኛ በሲዳማ ምድር ብቅ ያሉት ሲኣኖች በወቅቱ በርካታ ህዝብ በተከታይነት ማፍራታቸውን ኣስታውሳለሁ። የዛሬውን ኣያድርገውና ያን ጊዜ በርካታ ሲዳማዎች ኣንደኣለኝታቸው ኣድርገው ይመኩባቸው ነበር፤ ምንም እንኳን ህዝቡ የጠቀውን ያህል ምላሽ ሲኣኖች መስጠት ባይችሉም። ኣሁን ኣሁን ሲኣን ምን ያህል ኣባላት እንዳሉ መረጃው ባይኖረኝም፤ እንደምመስለኝ ከሆነ ኣገር ውስጥ ሆነው ከገዥው ፓርቲ ጋር የተኮረፉ ኣባላቱ ከእውነተኛ ኣባላቱ በቁጥር ሳይበልጡ ኣይቀሩም።

እኛ ኣገር ባህል ይመስል የፖለቲካ ፓርቲዎች የኣባላቸው ቁጥር የሚያውቁት ሳይሆን ለማወቅ ጥረት የሚያደርጉት ለምርጫ ብቻ ነው። ያነም ብሆን እነርሱ ወደ ህዝቡ ሄደው ሳይሆን በገዥው ፓርቲ የመልካምኣስተዳደር ችግር የተሰላቸው ህዝብ ነው እነርሱን ፍለጋ የሚሄደው። ይህ ስል ደግሞ እውነተኛ ከልባቸው ሲኣንን የምደግፉ ኣባላት የሉትም ማለት ኣይደለም።

የሲዳማ ህዝብ የተለያዩ በደሎች ሲደርሱበት ሽንጡን ገትሮ ከመከራከር ይልቅ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት የምቀናቸው ሲኣኖች፤ ኣንሰም በዛም በምድረ ሲዳማ ቢሮ ኖሮት፤ መሪዎቹ እነማን እንደሆኑ መንግስትም ህዝብም ኣውቆላቸው ያሉ ናቸው።

እስቲ ስለ ሌሎቹ የሲዳማ ፖለቲካ ድርጅቶች እናውራ። ከላይ ስማቸውን ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ከኣንድም ሁለት ከሁለትም ሶስት የሲዳማ የፖለቲካ ድርጅች ከውጭ ኣገራት ሆነው ይንቀሳቀሳሉ። ኣገር ውስጥ መንቀሳቀስ ምን እንዳስፈራቸው ባይታወቅም። እነዚህ ድርጅቶች የኣስራር ፊሎሶፊያቸው ምን እንደሆነ ባላውቅም ለሲዳማ ህዝብ መብት እንደምታገሉ በዌይብ ሳይቶቻቸው ላይ በለጠፏቸው መልዕክቶች ያሳወቁ ሲሆን፤ ኣላማቸውን በተመለከተ ኣንድም ጊዜ ወደምታገሉለት የሲዳማ ህዝብ ቀርበው ያስረዱበት ጊዜ የለም።

ለህዝብ የምታገል ድርጅት እንደ እኔ እምነት ከሆነ ከህዝብ ጋር መስራት ኣለበት። እርግጠኛ ነኝ የሲዳማ ህዝብ ስለ እነዚህ ለመብቱ እንታገልልሃለን የምሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ኣላማ የሚያውቅበት ሁኔታ ቢኖር ኖሮ በርካታው ህዝብ ድጋፍ ኣይነግፋቸውም። ታዲያ ምን ያደርጋል እነርሱ ከውጭ ኣገራት ሆነው ኢንቴርኔት ለማይጠቀም ህዝብ በኢንተርኔት መልዕክት ያስተላልፋሉ።

እንዴ እኔ ከሆነ የሲዳማ ህዝብ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልገዋል። የሲዳማ ዲያስፖራውም ቢሆን እዚያ ውጭ ኣገር ሆኖ ጡሩባ ከመንፋት ወደ ሲዳማላንድ ገብቶ ቢሮ ከፍቶ፤ ከምመለከተው መንግስታዊ ኣካል እውቅና ኣግኝቶ፤ ለህዝቡ መታገል ኣለበት። የድርጅቶቹም መሪዎች ብሆኑ ማንነታቸውን ለህዝብ ኣውጥተው ማሳወቅ የጠበቅባቸዋል።

ሌላው እንደ ሲዳማ የፖለቲካ ድርጅትነቱ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት የገዥው ፓርቲ ኣካል የሆነው የቀድሞው ሲህዴድ ኣሁኑ ደኢህዴን ነው። በርግጥ ደኢህዴን በሲዳማ ውስጥ ገዥው ፓርት ከመሆኑ የተነሳ ስር ሰደዋል። እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅሩን ዘርግቶ ኣባላቱን በመመልመል ብዙ ደጋፊዎችን እና ኣባላትን ኣፍርቷል። ድርጅቱ የሲዳማ ድርጅትነቱን ኣረጋግጣል።ደኢህዴን የሲዳማ ስም ነው እስከ መባል ደርሷል።

ሆኖም የዞኑ ደኢህዴኖች ተቃዋሚዎችን ኣያቀርቡም፤ ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ለህዝብ እንዲያስተዋውቁ እድል ኣይሰጡም፤ በራሳቸው ትንሽ የምቀሳቀሱ ብኖሩም የተለያየ ተለጣፊ ስሞችን እየሰጠ እንቅስቃሴታቸውን ያስተጓጉላል።በሲዳማ ህዝብ ዘንድ እኔ ብቻ ለወደድ፤ እኔ ብቻ ልስራ ይላሉ። ከተቃዋሚዎች ጋር ለመስራት እድል የሰጡበት ጊዜ የለም። በዞኑ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ በመሆኑ ኣንዳንዴ ወሳኝ የምባሉ ውሳኔዎችን ከወሰኑ በኃላ ወደ ህዝብ ያወርዳሉ። ማንኣለብኝነት ያጠቃዋል። የራሳቸውን ውሳኔ ህዝባዊ ለማስመሰል ጥረት ያደርጋሉ፤ ወዘተ የመሳሰሉትን ኣስተያየቶችን በደኢህዴን ላይ ማንሳት ይቻላል።በተለይ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በዞኑ ውስጥ በመሆን ላይ ካሉት ኣጋጣሚዎች መረዳት የምቻለው ደኢህዴን የህዝቡን የልብ ትርታ ማግኘት እንዳልቻለ ነው።

እንዳው በኣጠቃላይ ሳስበው የሲዳማ ፖለቲካ የህዝብ ፖለቲካ ሳይሆን የግለሰቦች ይመስለኛል። ምክንያቱም በተለይ ኣሁን በቅርቡ ከሲዳማ የክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ህዝባዊ ንቅናቄ በተመለከተ ከደኢህዴን በኩል ያሉት የሲዳማ ኣመራሮች ጥያቄው የግለሰቦች ነው በማለት በግለሰቦች ላይ ጣታቸውን ስቀስሩ የሲዳማ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ለጥያቄ ኣለመመለስ እንደተጠያቅ ኣድረገው የምያቀርቡት የደኢህዴን ኣመራሮችን ነው። ኣንደኛው ሌላኛውን ተጠያቂ እያደረገ ህዝቡ በመሃል እየተጎዳ ያለ ይመስለኛል። ለነገሩ ሁለቱም ኣካላት ጥያቄ የማን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል ብዬ ኣምናለሁ።

በኣጠቃላይ የሲዳማ ፖለቲካኞች ማለትም ተቃዋሚዎችን ይሁኑ በስልጣን ላይ ያሉት ለሲዳማ ህዝብ የምበጀውን ከማድረግ ወደ ኃላ ማለት የለባቸው። ከራሳቸው ጥቅም በፊት የቆሙለትን ህዝብ ጥቅም ማስቀደም መቻል ኣለባቸው። ዛሬ ኣንዱ ሌላኛውን በመሆን ላይ ባለው ጉዳዮች ላይ የምወነጃጀሉ ከሆነ ለህዝቡ ፋይዳ የለው። ህዝቡ መልካምኣስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱለት ነው የምፈልገው፤ ህዝቡ የምያነሳቸው ጥያቄዎች በኣግባቡ እንዲመለሱለት ነው የምፈልገው፤ የሲዳማ ህዝብ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ልማት እንዲጠናክርለት ነው የምፈልገው። እነዚህ ለውጦች ለማምጣት ያሏቸውን ልዩነቶች በመተው የህዝብን ጥቅም በማስቀደም እጅለእጅ ተያይዘው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ፈጣሪ ሲዳማን ይባርክ!
ቸር እንስንብት

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር