የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነርና ሁለት የዞን ፖሊስ አዛዦች ታስረው እንዲቀርቡ ታዘዘ የሲዳማ ዞን ፖሊስ መምርያ አዛዥም ይገኝበታል


በታምሩ ጽጌ
የፌዴራል ፍርድ ቤት ትዕዛዝን አላከበሩም በሚል የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ወይም ምክትል ኮሚሽነር፣ የጌዲኦ ዞን ፖሊስ መምርያ አዛዥንና የሲዳማ ዞን ፖሊስ መምርያ አዛዥን የፌዴራል ፖሊስ አስሮ የፊታችን ዓርብ እንዲያቀርባቸው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዘዘ፡፡ ፍርድ ቤቱ ኃላፊዎቹ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ያስተላለፈው ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነና ባልታወቀ መንገድ ሥራውን እንዲያቆም የተደረገው፣ በጌዴኦ ዞን ይሠራ የነበረው የሳማሪታንስ ፐርስ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ሠራተኞች ባነሱት የመብት ጥያቄ ጉዳይ መሆኑ ታውቋል፡፡

በድርጅቱ ላይ ክስ መሥርተው ለነበሩት አቶ ደረጀ ገብረ ማርያም፣ ወ/ሮ አቢጊያ ለገሰ፣ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ፣ ወ/ሮ ምህረት አበራ፣ አቶ ዮሐንስ አዳሙ፣ ወ/ሮ እመቤት ዓለሙ፣ አቶ አዲስ አበባና አቶ መስፍን ግዛው፣ የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንደየአገልግሎታቸው እንዲከፈላቸው ያስተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም፣ በድርጅቱ አካውንት ውስጥ ምንም ዓይነት ገንዘብ ባለመኖሩ፣ የድርጅቱ ንብረት መሆናቸው የተረጋገጡ ተሽከርካሪዎችን በመያዝና በሐራጅ ተሸጠው እንዲከፈላቸው ታህሳስ 27 ቀን 2003 ዓ.ም. ውሳኔ ማስተላለፉን የውሳኔው ግልባጭ ያስረዳል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ቆመው በተገኙበት የዞኑ ፖሊስ አዛዦች ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፍርድ አፈጻጸም መምርያ እንዲያስረክቡ በተደጋጋሚ ትብብራቸውን ቢጠየቁም ሊያቀርቡ ባለመቻላቸውና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲያስፈጽም ቢታዘዝም ተፈጻሚ ሊያደርግ ባለመቻሉ፣ ሦስቱም በፌዴራል ፖሊስ ታስረው ጥቅምት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ የፍርድ ባለመብቶቹ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሕግ በወሰነላቸው መብት ተጠቃሚ አለመሆናቸውንና በመጉላላት ላይ እንደሆኑም ፍርድ ቤቱ ጠቅሷል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8215-2012-10-24-06-22-42.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር