የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ስለምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁና ድርድር ምን ይላሉ?


‹‹የሥነ ምግባር አዋጁን ፈርመን ብንደራደር በግሌ ችግር የለብኝም›› አቶ ግርማ ሰይፉ (መድረክ)
‹‹እንደ ዜጋ አዋጁን አከብራለሁ አስገድደው ሊያስፈርሙን ግን አይችሉም›› ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (መድረክ)
‹‹አጠቃላይ መፍትሔ አምጪ ባይሆንም አንድ ዕርምጃ ነው›› አቶ ሙሼ ሰሙ (ኢዴፓ)
‹‹አዋጁን ፈርመን ብንቀበልም ያስከበረልን ነገር ስለሌለ ከጋራ መድረክ ወጥተናል›› አቶ ወንድማገኝ ደነቀ (መኢአድ)
በዮሐንስ አንበርብር የፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ የበርካታ ፓርቲዎች ይሁንታን አግኝቶ ከፀደቀ ሦስት ዓመታት ያለፉት ቢሆንም፣ ይህ የሥነ ምግባር አዋጅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሒደት ውስጥ ካበረከተው አስተዋጽኦ ይልቅ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ፈተና የሆነ ይመስላል፡፡ አንዳንዶቹ በአዋጁ ዙሪያ እርስ በእርስ አይግባቡም፤ ሌሎች ደግሞ አዋጁን ፈርመን የገባንበት የድርድር መድረክ ያመጣልን ነገር የለም ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተሳታፊ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥታቸውን አቋም ባለፈው ማክሰኞ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከመድረክ ፓርቲ ለቀረበላቸው የድርድር ጥያቄ የኢሕአዴግንና የሚመሩትን መንግሥት አቋም አሳውቀዋል፡፡

መድረክ ከኢሕአዴግ ጋር ለመወያየት በመጀመሪያ የሥነ ምግባር አዋጁን መፈረም አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የውይይት መድረኩ የተዘጋ ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ይህንን አስመልክቶ የመድረክ አመራሮችን ያነጋገርን ሲሆን፣ መድረክ በተሰጠው ምላሽ ላይ ተነጋግሮ አቋም ያለመያዙን ለመረዳት ተችሏል፤ አመራሮቹ ግን እርስ በርሳቸው በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም የተለያየ ነው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመድረክ ተወካይ የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ድርድር ለመጀመር የቀረበው ቅድመ ሁኔታ ያለው ትርጉም ውኃ የማያነሳ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት አዋጁን መፈረም ወይም አለመፈረም፣ አዋጁ ተገቢ ይሁንም አይሁን ከመቀበል ሊያድነን አይችልም ይላሉ፡፡

‹‹አዋጅ በመሆኑ ብቻ ይገዛናል›› የሚሉት አቶ ግርማ፣ አዋጁ ላይ ፈርሙ ብሎ ኢሕአዴግ እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ አስገራሚ ነው ብለዋል፡፡ መድረክ ከኢሕአዴግ ጋር ለመወያየት የሚፈልግ ከሆነና ኢሕአዴግ ይህንን ቅድመ ሁኔታ የማያነሳ ከሆነ ግን፣ አዋጁ ላይ ፈርሞ የሚበልጠውን ድርድር መጀመር አለብን የሚል የግል የፖለቲካ አቋም እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲያቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ስላለው አቋም ወደፊት የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል፡፡

የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፣ ‹‹የሥነ ምግባር አዋጁን እንደ ዜጋ ሕግ ስለሆነ ብቻ መቀበል ግዴታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እንወያያለን፣ እንደራደራለን ብለን እናስባለን፡፡ በዚህ ላይ መቼም ተስፋ አንቆርጥም፤›› የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፣ ‹‹ኢሕአዴግ እጃችንን ጠምዝዞ ሊያስፈርመን አይችልም በመሆኑም ቅድመ ሁኔታው እስኪነሳ እንጠብቃለን፤›› ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ ቃል በቃል ከውጭ ተሞክሮ የወሰድነው የሚለው ሰነድ በምርጫ ወቅት ፓርቲዎች ሊኖራቸው ስለሚገባ ሥነ ሥግባር ብቻ ነው የሚያወሳው፡፡ መድረክ ግን ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች ማለትም እንደ ምርጫ አስተዳደር ያሉ ጉዳዮች መካተት አለባቸው ብሎ ያምናል ሲሉ ዶ/ር ነጋሶ ይገልጻሉ፡፡

የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ በሥነ ምግባር አዋጁ ላይ ፓርቲያቸው ከፈረመ በኋላ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን የተቀላቀለ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘጠኝ አጀንዳዎች ተቀርፀው በሦስቱ ላይ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ፣ ቀሪዎቹ ስድስቱ ግን በእንጥልጥል እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በየሁለት ወሩ ቋሚ ስብሰባ እየተደረገ ሲሆን፣ ከዚህ የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ውጪ አስፈላጊ ናቸው በተባሉ ጉዳዮች ላይ በመገናኘት እንወያያለን ብለዋል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ገቢ ጉዳይ፣ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና በመሳሰሉት የተለያዩ ጉዳዮች ላይና በመገናኛ ብዙኅን አጠቃቀም እስከ ዛሬ ድረስ መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹አዋጁን በመፈረም የመሠረትነው የጋራ መድረክ ኢሕአዴግ እንደሚለው መሠረታዊ ችግሮቻችንን ሙሉ ለሙሉ የሚፈታ ሆኖ አላገኘነውም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በአጠቃላይ መፍትሔ አምጪ ነው ብለን አናስብም፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አንድ ዕርምጃ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሥነ ምግባር አዋጁን በመፈረም የጋራ ምክር ቤቱን ከተቀላቀሉት ፓርቲዎች መካከል መኢአድ አንዱ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ያለው አቋም ግን የተለየ ነው፡፡

የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ወንድማገኝ ደነቀ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት ኢሕአዴግ ራሱ የሥነ ምግባር አዋጁን በመጣስ ተስፋ ስላስቆረጣቸው ወዲያውኑ ከጋራ መድረኩ ወጥተዋል፡፡

የምርጫ ውጤት የሚገለጽበትን አግባብ የሥነ ምግባር አዋጁ የሚያስቀምጥ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ግን ይህንን በመጣስ ሕዝብ ሰብስቦ አሸንፌያለሁ በማለት አዋጁን የጣሰ ተግባር ፈጽሟል ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በ23 ጥይት ተደብድባ ስለተገደለች አባላችን ጉዳይ ለማጣራት በጋራ መድረኩ ያደረግነው ጥረት የታፈነ በመሆኑ አቋርጠን ወጥተናል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ስለጉዳዩ ተጠይቀው፤ ኢሕአዴግ የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁን ለድርድር እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው፣ ፓርቲዎች ከፈረሙ በኋላ በምርጫ ወቅት ችግሮች ቢከሰቱ ያለመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንዲስተካከሉ ሆን ብሎ ያወጣው አዋጅ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ከመድረክ ጋር ባለው እሰጣ አገባ ኢሕአዴግ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡ ጉልበት ያለው መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል፡፡

መድረክ ለመፈረም ፈቃደኛ ያልሆነበት ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን የፖለቲካ ኪሳራ ያስተዋለ ነው የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ፣ መድረክ ቀደም ሲል አልፈርምም ብሎ አሁን ቢፈርም የፖለቲካ ኪሳራው የከፋ ስለሚሆንና ከደጋፊዎቹ ጋር ላለመጋጨት በሚል ሥጋት ነው ብለዋል፡፡

የፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን በተመለከተ በተለይ በኢሕአዴግና በመድረክ መካከል አልቋጭ ያለው ውዝግብ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሁለቱ መራኮቻ አድርጎታል ሲሉ የሚገልጹም አሉ፡፡  
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8210-2012-10-20-13-24-15.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር