“መልካም አስተዳደርን ያላካተተ ልማት ልማት አይባልም”


በምሕረት ሞገስ
ኢትዮጵያ በልማቱ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ታስመዝግብ እንጂ ዴሞክራሲን በማስፈን ወደኋላ እንደቀረች የተለያዩ የሰብአዊ መብትተሟጋች ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ኢሕአዴግም ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንሥቶ ትችት ሲሰነዘርበት የቆየው ዴሞክራሲን ማስፈን ባለመቻሉ ነው፡፡

መንግሥት ዴሞክራሲን ለማስፈን ብዙ ትኩረት ባለመስጠቱ የበላይና የበታች እንዲኖር፣ ፍትሕ እንዲዛባ በአጠቃላይም የመልካም አስተዳደር እጦት በአገሪቷ እንዲስፋፋ አድርጓል በሚልም ይተቻል፡፡ 

አቶ አሰፋ አደፍርስ በአሜሪካ ለ39 ዓመታት ኖረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በልማቱ ዘርፍ ከተሰማሩም ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በሥራ አጋጣሚ የሚያስተውሉት የመልካም አስተዳደር እጦት ግን አገሪቷን ወደኋላ የጐተተ፤ እሳቸውና ሌሎች ባለሃብቶችም የተሰማሩባቸውን የተለያዩ የልማት ዘርፎች ከሚፈለገው ደረጃ እንዳይደርስ ማነቆ የሆነ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት በተንሰራፋበት ሁኔታ የሚታይ የኢኮኖሚ ዕድገትም በሕዝቡ ኑሮ ላይ ለውጥ እንደማያመጣም ይናገራሉ፡፡

ከሚኖሩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በአገሪቱ ለውጥ ማየታቸውን፤ ሆኖም ለውጡ መሳጭ አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ አሰፋ “አገር ውስጥ ያለውም ሆነ ከውጭ የሚመጣ ባለሀብት ሕንጻ ሊሠራ ይችላል፡፡ ሕንጻ ስለተደረደረ ግን ልማት ለማ ማለት አይደለም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከሕዝቧ በላይ ሊያስተዳድር የሚችል ሀብት አላት፡፡ ሆኖም በየመንገዱ የሚለምን እናያለን፣ ልጃቸውን አዝለው የሚበሉት የሚጠይቁ ይታያሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ከመልካም አስተዳደር እጦት በሚመነጭ ችግር ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን ያላካተተ ልማት ልማት አይባልም፤” ብለዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ያለው ችግር አሁን የመጣ ሳይሆን የቆየ ሊሆን ይችላል፡፡ በደርግ ጊዜ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አሁን መሻሻል አለ፡፡ ሆኖም መሻሻሉ አገሪቷ ውስጥ ካለው ሰላምና የመሥራት እድል ጋር ሲነጻጸር ያነሰ ነውም ብለዋል፡፡

አቶ አሰፋ እንደሚሉት፤ በሥራ አጋጣሚ የሚያዩት ሙስና መስፋፋቱን፣ አድሎአዊ አሠራር መኖሩን ነው፡፡ አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልጉም የሚባለውን ሁሉ አሜን ብሎ ተቀብሎ መሔድ እንጂ ትክክል አይደለም ብሎ የሚናገር መሥራት የማይችልበት ሁኔታ መኖሩን ነው፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዕረፍት በኋላ በኢትዮጵያ በልማቱ የተሰማሩና ለሐዘን ብለው የመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቤተ መንግሥት ተገኝተው ሐዘናቸውን በገለጹበት ወቅት ያገኘናቸው አቶ አሰፋ፣ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ፤ የነበረው አሠራር መልካም፣ ዴሞክራሲውም የተረጋጋ እንደሆነ ተደርጐ የሚነገረው ትዝብት ላይ የሚጥል ነው ብለዋል፡፡ ይልቁንም የተበላሹ አሠራሮችን አስተካክሎና የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን አጠናክሮ አገሪቷን በዴሞክራሲውም ሆነ በኢኮኖሚው ግንባታ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

“አሠራሮች የሚሻሻሉ ከሆነ፣ ሰውም የሚያየው የአሠራር ግድፈት ላይ በግልጽ አስተያየት የሚሰጥበት ሁኔታ ከታመቻቸ ጥሩ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ልማት ትርጉም የለውም፡፡ እኔ የማየው ሰዎች እንደልባቸው እንደማይናገሩ ነው፡፡ ይህ እያለ አገሪቱ ለምታ ሔዳለች ማለቱ ልማት አይመስለኝም፡፡ ልማት የምንለው የሰው ልጅ እኩል የመናገር፣ እኩል የመጻፍ፣ እኩል የመስተናገድ፣ እኩል አገልግሎት የማግኘት፣ እኩል የመሥራት እድል ሲኖረው ነው፤” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊ አገር አለኝ ብሎ እንዲኖር የሚኖርበት መሬት ሊኖረው ይገባል የሚሉት አቶ አሰፋ፣ አቶ መለስ በአንድ ወቅት “የአንድ ሰው ንብረት ጣሪያና ግድግዳ ነው” ያሉትን አይስማሙበትም፡፡ አንድ ሰው አገሬ ብሎ እንዲኖር የሚያደርገው “የኔ” የሚለው የሚኖርበት መሬት ሲኖረው ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም የሚመጣው መንግሥት ይህንን አሻሻሎ የሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄ የሆነውን መሬት በሚገባው ልክ ሊፈቅድለት ይገባል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡

“አቶ መለስ በጣም አዋቂ ሰው እንደነበሩ ይገባኛል፤ ዋሽንግተን በመጡ ጊዜም አነጋግሬያቸዋለሁ፤” የሚሉት አቶ አሰፋ፣ ሆኖም በሚነገረውና በሚደረገው መካከል ሰፊ ልዩነት ስላለ መስተካከል አለበት ይላሉ፡፡ “የአንድ ኅብረተሰብ ክፍል ታላቅ ሆኖ ሌሎች ታናሽ የሚሆኑበት ምክንያት የለም፡፡ ሁሉም እኩል መሆን አለበት፡፡ ኢኮኖሚውም ሰው በሠራ መጠን ማደግ አለበት፡፡ አንዱ ክፍል ብቻ ባለቤት፣ ኃያልና ፈላጭ ቆራጭ ከሆነ አገር አትለማም፤ ሁላችንም የምንሳተፍበት መንገድ ከመጣ ትክክል ይሆናል፡፡ ሥልጣን የሚወስድ መግሥት ኢትዮጵያውያን ተባብረው እንዲሠሩ ማድረግ አለበት፤” ብለዋል፡፡

አቶ መለስ እስካሁን ከሠሩት ሥራ ጥሩም መጥፎም አለ፡፡ ጥሩውን ይዘን መጥፎውን ማረም አለብን የሚሉት አቶ አሰፋ፣ በተለይ ኢትዮጵያዊው የተለያየ አመለካከት ቢኖረውም በኢትዮጵያዊ አንድነቱ አምኖ የአገሪቷ ልማት የሚፋጠንበትንና ከአገሪቷ ሀብት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር ማስፈን ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል፡፡

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ልማት የሚጠበቅበትን በተመለከተም የመጣው ዳያስፖራው ሁሉ ሥራውን በትክክል ይሠራል ወይ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ለልማት ብሎ ከውጭ የመጣ ሰው በሚሠራበት አካባቢ የመልካም አስተዳደር እጦት ሰለባ እየሆነ፣ የሚሠራበት አካባቢ ተወላጅ ካልሆነ ንብረቱ እየተዘረፈ፣ እየተቃጠለ፣ አትሠራም እየተባለ የሚሰቃይበት መልክ መኖሩ መቀየር አለበት ብለዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ ያፈሰሱትን ንብረት ትተው ወደ ስደት የተመለሱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚመለከተው ክፍል አገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ከውጭ ከሚመጡት ጋር አስተባብሮ ልማት የሚመጣበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡  

እንደ አቶ አሰፋ አነጋገር ሙስና ከማዘጋጃ ቤትና ከመንግሥት ባለሥልጣናት ይጀምራል፡፡ ይህንን ሳያሻሽሉ ነፃነት አለ፣ ሰላም ነው፣ አገር ለምታለች የሚባለው ትክክል አይደለም፡፡ አሠራሮችን ቀይሮ ሕዝቡ የአገሪቷ ሀብት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መቀየስ የመጪው መንግሥት የቤት ሥራ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር