አዲሱ የዓለም ኢኮኖሚ ጨዋታ ለአፍሪካና ለምዕራቡ ዓለም ስጋት



በብርሃኑ ፈቃደ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ፖለቲካው ሁሉ በኢኮኖሚ ባለሙያዎችም ዘንድ የሚወናጨፍ ፖለቲካ ቀድ አገላለጽ መንሰራፋት ይዟል፡፡
በተለይ የኃይል ሚዛኑ በእስያዎቹና በምዕራባውያኑ ዘንድ በሚያሻኩትበት በዚህ ዘመን፣ አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ፣ በኢኮኖሚ ኒዮ ኢምፔሪያሊዝም አዙሪት እየተናጡ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ አንስተው ሞቅ ያለ ውይይት የሚያነሱና ጣት የሚቀስሩ ዲፕሎማቶች (ያውም ከእስያውያኑ ጎራ ሆነው) ሩቅም ሳይኬድ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡

አንዳንዶች  ደግሞ የ‹‹ጂኦ ኢኮኖሚክስ›› ንድፈ ሐሳብን ቀምረው ቱባ መጻሕፍትን እያወጡ በማስነበብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ባለንበት የነጮቹ ዓመት ተጽፎ ለንባብ የበቃውና ክላውስ ሶልበርግ ሶይለን በተባሉ የኢኮኖሚ አዋቂ የተጻፈው መጽሐፍ የመግቢያ ቅኝቱን ከጂኦ ፖለቲካ ወደ ጂኦ ኢኮኖሚ የተደረገውን ጉዞ የሚያመላክት ነው፡፡

እንደ ጸሐፊው ገለጻ፣ ጂኦ ኢኮኖሚክስ በባህል፣ በቦታ እንዲሁም በውሱን ሀብቶች ስትራቴጂካዊነት ላይ የሚያነጣጥርና ለዚሁም ዓላማው በዘላቂነት ላይ የተመሠረተና ተወዳዳሪ ጥቅምን ለማግኘት ሲባል የሚካሄድ ድርጊትን የሚያጠና ክፍል ነው፡፡ በጂኦ ፖለቲካዊ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ተንጠላጥሎና በዘመነ ግሎባላይዜሽን እየተተገበረ ያለ የኢኮኖሚክስ ዘርፍ እንደሆነም ይናገሩለታል፡፡ ይህም ሲባል ግን ከጂኦ ፖለቲካ የሚለይባቸው ሁለት መሠረታዊ መስኮች አልታጡም፡፡ እንደ ርዕሰ ጉዳዩ ሲያዩት ፖለቲካና ወታደራዊ ኃይል ላይ ከማተኮር ይልቅ ኢኮኖሚያዊ ኩነቶችን መምረጡ ከጂኦ ፖለቲካዊ እንዲለይ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ተውኔቱን የሚከውኑት ተዋንያኑ አገርን የሚወከሉ ግለሰቦች ሳይሆኑ የግል ዘርፉ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩና ጅማሬም ፍጻሜያቸውም ለሚሠሩበት ተቋም ባለቤቶች ታማኝ መሆን ነው፡፡

ምንም እንኳ የየአገሮቹ ሹማምንት ግንባር ቀደምቴዎች አይሁኑበት እንጂ በጂኦ ኢኮኖሚ አጥኚዎች ዘንድ የአገሮች ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት አግባብ የሚጠናበት መሆኑ የሚመሰከርለት ይህ የኢኮኖሚ ክፍል፣ በልዕለ ኃያል አገሮች ዘንድ ከሚመጣው የጥቅም ፍላጎት አኳያ አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ፣ እስያ፣ ምንም እንኳ የእነዚህን ያህል አይሁን እንጂ አሁን አሁን ምዕራባውያኑም በመጤዎቹ ኃያላን ክንድ ሥር እየወደቁ ስለመምጣታቸው የዚህ ዘርፍ አጥኚዎች ብቻ ሳይሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም እያመነ ይመስላል፡፡ ከእነዚህ መጤ ኃያላን መካከል ቻይና ቀለመደማቅ ሆና ትጻፋለች፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት፣ ሴፕቴምበር ወር መጨረሻ ላይ ተመድ አፍሪካውያን ‹‹ከደቡባዊ የልማት አጋሮች›› ጋር የሚያደርጉትን ትብብርና ቁርኝት በተባበረ ስትራቴጂና ቁጥጥር በታከለበት ግንኙነት ይሆን ዘንድ ሲያሳስብ፣ እነዚህን አገሮች ልትጠነቀቋቸው ይገባል ብሎ ነበር፡፡ ቻይና፣ ህንድ፣ ብራዚል፣ ደቡብ ኮርያ እንዲሁም ቱርክ ከአፍሪካ ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ለተመድ ስጋት ለምን ሆነ ቢባል፣ አፍሪካውያኑ ከተጠቀሱት አገሮች ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት እጅግ እያሻቀበ በመገኘቱ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1990 የነበረው የ8.8 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ የንግድ ግንኙነት እያደገ መጥቶ በ2007 148 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም አፍሪካ በብዛት ሸማች የሆነችበት ግንኙነት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ቻይና ከንግድ ባሻገር ተፅዕኖ መፍጠር የቻለችበት አጋጣሚም እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2009 በነበሩት ዓመታት ተስተውለው እንደነበር ተመድ ዋቢ ሲያደርግ፣ የእዳ ቅነሳ የተደረገላቸውን 31 አገሮች በማመላከት ነው፡፡ ለእነዚህ አፍሪካውያን የ2.57 ቢሊዮን ዶላር እዳ ቀርቶላቸው እንደነበር አስቡት እንጂ፣ ለመክፈል አታስቡ ተብለዋል፡፡

ይህንን ያየው ተመድ አፍሪካ በመመንደግ ላይ ላሉ መጤ የኢኮኖሚ ኃያላን ላይ ‹‹የምትከለተው ስትራቴጂ የላትም፣ አንዳንድ መጤዎቹ ግን አላቸው›› ያለው ተመድ፣ በአዲሱ ዘመነ ጂኦ ኢኮኖሚ፣ ምንም እንኳ አፍሪካውያን በቅናሽ ዋጋ የፍጆታ ዕቃዎችን ቢሸምቱ፣ የጋርዮሽ (ሽሙር) ንግድና የፋይናንስ ድጋፎች የመንግሥታቱን ገቢ ቢያሳብጡም መጤዎቹ ኃያላን የአፍሪካን ኢንዱስትሪ በተለይ ማኑፋክቸሪንግና የግንባታ ዘርፎች አዳክመዋልና አስቡበት ብሎ ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካ ያገሬው ኩባንያዎች በቻይናውያኑ አቅምን ያላገናዘበ ውድድር፣ ከሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ገበያው ሹልክ እንዲሉ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ እንደ አፍሪካ ኅብረት ያሉ ተቋማት፣ ከተመድ ጋር በመሆን ከመጤዎቹ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ላይ የመደራደር አቅማቸውን በማሳደግ ሊረዷቸው እንደሚችሉ ተመድ ራሱ ይመክራል፡፡ ለአብነትም ስትራቴጂያዊ ጥናትና ትንተና በመስጠት ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ተመድ ሲመክር፣ መጤዎቹንም ነካ ያደርጋል፡፡ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለረጅም ጊዜ ለመጠቀም ስትመጡ የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል አድርጉ ብሏቸው ነበር፡፡

ጂኦ ኢኮኖሚስቶች አፍሪካ በጠራራ ፀሐይ ተዘርፋለች ወደሚል ድምዳሜ የሚያመራ ምርምር ይፋ እያወጡ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ ፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጆርናል፣ በቅጽ 4፣ 2010 አካቷቸው ከነበሩ ልዩ ልዩ ጥናቶች ውስጥ ቻልዲያንስ ሜንሳህ በሳይኖ አፍሪካ ላይ ከጂኦ ኢኮኖሚና ከቻይና የሦስተኛው ዓለም አጋርነት ተራማጅ አስተሳሰብ ጋር አሰላስለው ያጠኑት አንዱ ነበር፡፡

ሜንሳህ እንደሚገልጹት፣ ቻይና ለኢኮኖሚዋ ኃይል ሞተር በሆነው ግን ደግሞ በማይጠረቃው የጥሬ ዕቃ ፍላጎቷ እያቀጣጠለች መምጣቷ አዲስ የኃይል ሚዛን እንዲፈጠር ከማድረጓም በላይ፣ ይኸው ፈርጣማነቷ፣ በአፍሪካ ላይ ፈጣንና መወላወል የማያውቅ የውጭ ፖሊሲ እንድትከተል አደርጓታል፡፡ ቻይና በአፍሪካ ላይ የምትከተለው ጂኦግራፊያዊ ስትራቴጂ ተኮር ፖሊሲ፣ በዓለም ላይ ከዘረጋችውና ‹‹Going Global Strategy›› ብላ ከሰየመችው ጋር የሚግባባ መሆኑን አጥኚው ይናገራሉ፡፡

ይህ ፖሊሲዋ ከዚህ ቀደም ትከተለው ከነበረውና የአሜሪካን በላይነት ለማሳጣት ታደርገው ከነበረው ፖለቲካዊ አካሄድ ያፈነገጠ መሆኑ ሲነገርለት፣ በዚህ ዘመን እንዲታይላት የምትፈልገው አፍሪካ ዘመም አካሄድ፣ የሦስተኛው ዓለም ንቅናቄን ደጋፊና ወዳጅ መምሰል ነው፡፡ የአዲሱ የቻይና መሠረታዊ አካሄድ ያልተቆጠበ የኃይልና ሌሎች የግብርና ሸቀጦችን አቅርቦት ለማረጋገጥ ነው የሚሉት እኒህ አጥኚ፣ እግረ መንገዷንም ከታይዋን ጋር የሚደረግ ወዳጅነትን ለመግታት ያለመ የዲፕሎማሲ ቀመር አበጅታለች ይሏታል፡፡

የጂኦ ኢኮኖሚ ተንታኞች መስማሚያቸው አንድ ነጥብ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም አፍሪካውያን ከታቀፉት መጠነ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት የድርሻ የድርሻውን ለመውሰድ የሚኳትን መንግሥት እየተበራከተ መምጣቱንና በዚህም ሳቢያ የዘረፋ ያህል ወይም የቀድሞውን የቅኝ አገዛዝ በሚተካከል አግባብ ቻይና አፍሪካ ላይ ተንሰራፍታለች የሚሉ ቢበረክቱም፣ ቻይና ግን ቢያንስ ቢያንስ ይህንን አባባል ውድቅ የሚያደርግ የብልጥ አካሄድ አላጣችም፡፡ በውስጥ ጉዳችሁ ምን አግብቶኝ? ማለቷ ከምዕራቡ ዓለም ሌላ የትችት በትር እንዲነሳባት አድርጓል፡፡ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ጉዳዬ አለማለቷን ይተቹታል፡፡

የሆነ ሆኖ ቻይናም ለአፍሪካ አፍሪካም ለቻይና አንዱ በማንኪያ አንዱ ባካፋ ሰጭና ተቀባይ ስለመሆናቸው፣ ቢያንስ እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ እስካሁን ያለውን የዓለም ኢኮኖሚ ዝቅጠትና የቻይናን ሁኔታ እያመሳከሩ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ አፍሪካ ለቻይና የጥሬ ዕቃና የተፈጥሮ ሀብት አቅራቢ ብቻ ሳትሆን፣ በገፍ ለሚመረቱ የቻይና ሸቀጦች ተቀባይና ማራገፊያ መሆኗ ጭምር ሌላው ዓለም በቀውስ ሲናውዝ፣ ቻይና የማያቋርጥ የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ የረዳ ግንኙንት ፈጥሯል ይላሉ፡፡

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ አፍሪካ ላይ የሚያራምደው ፖሊሲን በሚመለከትም የሚጻፉት ነገሮች ከዚሁ ከጥቅም የራቀ ቅኝት የላቸውም፡፡ በታሪክ ተሞክሮም ሆነ በጋራ ትግል ያደጉ ካፒታሊስቶች አፍሪካ ላይ፣ ሦስተኛው ዓለም ላይ የሚያደርጉትን ኢኮኖሚያሚ ተፅዕኖ እንደሚገታ አጋር ቻይና ራሷን ትመለከታለች ይሏታል፡፡ ይህ አካሄዷ ደግሞ ከቀዝቃዛው ጦርነት ተበራክቶ የቀጠለ እንደሆነ ሲነገርለት፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ‹‹ደቡብ ለደቡብ ትብብር›› (South South Cooperation) ጎልቶ ይወጣ ጀመር፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ግንኙንት እነ ጃፓንም ተሳታፊ ቢሆኑና በገንዘብ፣ በቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም በሥልጠና ዙርያ ትብብራቸውን ከአፍሪካ ጋር ቢመሠርቱም፣ የቻይናን ያክል የቱባ ድርሻ ይዘው በሰፊው አልተራመዱም፡፡ ለአብነት ጃፓን አፍሪካ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ2008 እዚያው ጃፓን ውስጥ ሲካሄድ፣ የአራት ቢሊዮን ዶላር ብድር ለአፍሪካ መስጠቷን ብታውጅም፣ በዚያው ዓመት ህንድም ለአፍሪካ አምስት ቢሊዮን ዶላር ብድር ሰጥታለች፡፡

ከአፍሪካ ባሻገር
የዓለም የማኅበራዊ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ በጂኦ ኢኮኖሚና በስትራቴጂ ፕሮግራሙ ይፋ ካደረጋቸው ጥናቶች መካከል በዚህ ፈረንጆቹ ዓመት ‘A New Era of Geo-economics: Assessing the Interplay of Economic and Political Risk’ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ አውደ ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ ርዕሱ የተጠቀሰውን ጽሑፍ ያቀረቡት ለብሉምበርግ ቴሌቪዥን የኢኮኖሚ ወኪል ዘጋቢዋና፣ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሊንዳ ዩህ ናቸው፡፡ የዓለም 20 በመቶ ሕዝብ የሚወክሉ ዜጎች ያሏት ቻይና፣ ለዓለም የዋጋ ግሽበት አለመረጋጋት መንስዔ እየሆነች መምጣቷን ጽፈዋል፡፡ የንግድ መጠኗ ላደጉትም ሆነ ላላደጉ አገሮች ሠራተኞችና ኩባንያዎች ስጋት እየሆነ ከመምጣቷ ባሻገር፣ ለኃይል ያላት ጥም የማይቆርጥ ፍላጎት የግጭት መነሻ ሰበብ ከመሆን አልፎ እንደ አሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም ላሉ አገሮች ባላንጣ እስከመሆን ደርሳለች ይሏታል፡፡ ለታዳጊና ድሀ አገሮች ደግሞ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ከመሆን ባሻገር ይህ ኢንቨስትመንቷ ለአንዳንድ አገሮች የኢኮኖሚ ደኅንነት እያስገኘ መምጣቱን ሊንዳ ጽፈዋል፡፡

የቻይና ተፅዕኖ ጎልቶ የታየው በሸቀጦች ዋጋ ላይ ነው የሚሉት ሊንዳ፣ በአገሪቱ ማሻሻያ መካሄዱን (እ.ኤ.አ. 1990) ተከትሎና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዘርፎች መስፋፋታቸው የአገሪቱን ኢንዱስትሪያዊ ጉዞ አፋጥነዋል ይላሉ፡፡ በመሆኑም ከአሜሪካ ቀጥላ የዓለም ሁለተኛ ነዳጅ ተመጋቢ አገር ስትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2004 የዓለም ጠቅላላ ኢኮኖሚ 4.4 በመቶ ከመሸፈን አልፋ፣ 30 በመቶውን የዓለምን የብረት ጥሬ ዕቃ፣ 31 በመቶ ከሰል፣ 27 በመቶ ብረትና 25 በመቶ አልሙኒየም ለፍጆታዋ አውላለች፡፡  በየጊዜው እየሰፋና እየተለጠጠ የመጣው የቻይና የጥሬ ዕቃ ፍላጎት እንደ አንዳንድ ገማቾች እምነት የዓለም የሸቀጥ ዋጋ በ50 ከመቶ እንዲጨምር ሰበብ የሆነ ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር በውጭው ዓለም፣ ባለፈው ዓመት ብቻ የ11 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አካሂጃለሁ ያለችው ቻይና፣ ኩባንያዎቿን (የመንግሥትም የግልም) ጥቅም ይገኝባቸዋል ባለቻቸው ክፍለ ዓለማት ሁሉ እየዘራች ወደ ዓለም በመሄድ ጉዞዋ እየተሳካላት ትገኛለች፡፡

ይህ ሁሉ ግን በአፍሪካውያን  ላይ ተረማምዳ እያደረገች ያለችውና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በስመ ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት አስፋፍታለች እየተባለች ብትወቀስም፣ ሰሚ ጆሮ የላትም፡፡ በወዳጅነት ላይ የተመሠረተና አገም ጠቀምም መርህ ባደረገ አካሄድ የማደርገው ነው የሚል መከራከርያ ታቀርባለች፡፡ 

ከአፍሪካ ባሻገር አሜሪካም በቻይና እየተዘረፈች ስለመሆኗ ትናገራለች፡፡ ፎርካስት ግሎባል በተሰኘ መጽሔት ላይ ጁዋን ዛራቴ የተባሉ ጸሐፊ፣ ‹‹Playing a New Geo economic Game›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ ቻይናና ሩስያ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አገሮችም የጂኦ ኢኮኖሚ አዲስ ጨዋታ እያንቀረቀቡ፣ ብሔራዊ ጥቅም ለማግኘት ርብርብ መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በግዙፍ ኩባንያዎቿ አማካይነት የዓለምን ገበያ መቆጣጠሯን የሚገልጹት ጁዋን፣ በተለይም የሶላር፣ የነፋስ እንዲሁም የከፍተኛ ፍጥነት ባቡር መስመር ዝርጋታ ገበያን በዓለም ደረጃ የተቆጣጠረችው ቻይና መሆኗ የጂኦ ኢኮኖሚ ጨዋታን በበላይነት እንድትመራ አስችሏታል ይላሉ፡፡

አሜሪካ ለአዲሱ የጂኦግራፊያዊ ኢኮኖሚ ስልት ዝግጁ አይደለችም የሚሉት ጁዋን፣ ሆኖም የአሜሪካ ኢኮኖሚ ደኅንነትን ለማምጣት ሲባል ፖለቲካን ከኢኮኖሚ ፍላጎት ጋር ማቀላቀል ተገቢ ስለመሆኑም ሆነ አይደለም ለማለት ጊዜው አይደለም ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ በድሆች ላይ ተንጠልጥለን አናተፍርም፡፡ ምሳሌው ደግሞ በኢራቅና አፍጋኒስታን ያደረግነው ነው፡፡ በዚያ ደኅንነትና ተግባራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማምጣት ሲባል የአሜሪካ ደምና ሀብት ፈሷል፡፡ ነግር ግን የአሜሪካ ኩባንያዎችና ጥቅሞቻቸው ገሸሽ ተደርገዋል፡፡ በአንፃሩ የቻይናውያን፣ የሩስያውያንና የሌሎች አገሮች ኩባንያዎች ግን ከነዳጅ፣ ከማዕድናና ከሌላውም ዘርፍ ትርፍ አጋብሰዋል፤›› በማለት ቁጭት አዘል አሜሪካዊ ትንተና ሰጥተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አገራቸው የቻይና ኢኮኖሚያዊ ዝርፊያ እንዳስቸገራትና በርካታ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶቿ የቻይና ሲሳይ እየሆኑባት መቸገሯን አሳስበዋል፡፡ የጁዋን ጹሑፍ ከሳይንሳዊ ምልከታና ትንታኔ ይልቅ አሜሪካውያንን የእስካሁኑ ትምህርት ይሁናችሁና ለዛሬም፣ ለነገም ተነሱ የሚል አንድምታ ያለው ቢመስልም፣ እኛ እንደ እነሱ አይደለንም፣ የዓለም የነፃ ገበያ መራሄነታችንን ማስጠበቅ፣ የካፒታሊስት ሥርዓት ማስቀጠያ፣ የግሉ ዘርፍ ነፃነት ማረጋገጫና የአሜሪካ ሥነ ምግባርን የሚያከብር የንግድ ትግበራ እንከተላለን በማለት አሳርገዋል፡፡

ከማምረቻ ዋጋቸው በታች የሚሸጡ የቻይና ሸቀጦች አፍሪካን ስለማጥለቅለቃቸው አንድ ወቅት ከፍተኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የነበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም፣ ከተኛችበት ድንገት የባነነችውና ፀረ ርካሽ ምርቶች ሕግ ለማመውጣት የተንቀሳቀሰችው የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርዶን ብራውን ጋር ሆነው ከተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ያደረጉት የነበረውን ውይይት በቢሯቸው ቻይናውያኑ በተከሉት መሣርያና ቴክኖሎጂ ውይይቱን ማካሄድ ባለመቻላቸው ወደ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አቅንተው በዚያ ውይይቱን ለማካሄድ እንደተገደዱ የውስጥ ምንጮች ያረጋግጣሉ፡፡ ሁሉም የመንግሥት ትልልቅ መሥርያ ቤቶች የቪዲዮ ኮንፈረንስ ማካሄጃ የተገጠመላቸው የስብሰባ አዳራሾችን የተከሉ ሲሆን፣ ምንጩ ደግሞ የቻይና ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ሆኖም ቻይናውያኑ ቤተ መንግሥት ድረስ ሰተት ብሎ ለገባው ርካሽ ቴክኖሎጂያቸውና ለተከሰተው አሳፋሪ ጉዳይ ግን ማንም ምንም ያለ የለም፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/business-and-economy/296-business-and-economy/8057-2012-10-13-11-00-21.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር