ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የግብርና ምርምር የጥራት ላቦራቶሪ ተከፈተ

አዲስ አበባ መስከረም 12/2005/ዋኢማ/-የግብርና ምርምር የጥራት ላቦራቶሪ ኢትዮጵያ በግብርና ምርቷ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት የግብርና ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው አስታወቁ።  � 

ሚኒስትሩ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤት ቅጽር ግቢ በዘመናዊ መሣሪያ የተደራጀውን ላቦራቶሪ ትናንት መርቀው ሲከፍቱ እንደተናገሩት፤ ላቦራቶሪው ግብርናውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያሸጋግርና የሀገራችንን ግብርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥራት መስፈርት እውቅና ለማግኘት የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው። ላቦራቶሪው አርሶ አደሩንም ሆነ አርብቶ አደሩን እንዲሁም መላ ሀገሪቱን ተጠቃሚ ያደርጋል። ይህም የግብርና ዕድገት ያፋጥናል።  � 

እንደ አቶ ተፈራ ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቱ የግብርና ምርት እንዲያደግ አዳዲስ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ላቦራቶሪውም ለቀጣይ እድገቱ አስተዋጽኦ በእጅጉ የጐላ ነው።

ለግብርናው ዘርፍ እድገት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በዘርፉ የተቀመጠው ግብ ስኬታማ ይሆን ዘንድ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ጀኔራል ዶክተር ሰለሞን አሰፋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ላቦራቶሪው በግብርናው ዘርፍ ለሚደረገው ጉዞ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። የሀገሪቱንም እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የምርቶችን የጥራት መስፈርት ማሟላት አጠያያቂ አይደለም። ለምርት ጥራት መረጋገጥ ደግሞ ላቦራቶሪው ዓይነተኛ ሚና አለው።

ላቦራቶሪው በስድስት ወራት ውስጥም ዓለም አቀፍ እውቅና እንደሚያገኝ ጠቁመው፤ ዓለም አቀፍ እውቅና የሚያገኛው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።   � 

እንደዶክተር ሰለሞን ገለፃ፤ የአርሶ አደሩን የተመራማሪዎችን ብሎም የሀገሪቱንም አቅም ያጎለብታል። ሀገሪቱም በግብርና ምርቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ያስችላታል።  � 

የኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ጌትነት አሰፋ በበኩላቸው፤ «ላቦራቶሪው በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን እቅድ ስኬታማ ለማድረግ ቁልፍ መሣሪያ ነው» ብለዋል።  � 

የግብርና ምርታማነትንም ከእጥፍ በላይ እንደ ሚያሳድግ ጠቁመው፤ ከምርታማነትም ባሻገር ጥራቱ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ ገበያ የሚፈልገው ጥራት ያለው ምርት መሆኑን ጠቅሰው፤ ገበያው በሚፈልገው ደረጃ የሀገሪቱን ምርት ለማቅረብ የላቦራቶሪው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።  � 

በኢንስቲትዩቱ የተደራጀው ሙዚየም በውስጡም የምግብ፣ የጥራጥሬ፣ የቅባት፣ የእንስሳት መኖ፣ የአትክልት ዝርያ፣ የደን ምርምር፣ የቡናና ቅመማቅመም፣ የመዓዛማ መድኃኒት ሰብሎች እንዲሁም የዓሳና የውሃ ውስጥ ህይወት ቴክኖሎጂንም ያካተተ ነው።

ለጐብኚዎቹ ገለጻ በተደረገበት ወቅት በሀገሪቱ 33 የጤፍ፣ 37 የቡና እንዲሁም 110 የስንዴ ዝርያዎች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር