ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግ ያቀረበው የትብብር ጥሪ አሳታፊ እንዲሆን አሳሰቡ

New

በየማነ ናግሽ
የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ ስብሰባውን አጠናቆ አዲሱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ከመረጠ በኋላ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ጋር መተባበር እንደሚፈልግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ጥሪውን በበጎ ጎኑ የተመለከቱ ተቃዋሚዎች ለተግባራዊነቱ ኢሕአዴግ ቁርጠኛ እንዲሆንና “የጋራ ምክር ቤት” በሚል ብቻ የተወሰነ እንዳይሆን አሳሰቡ፡፡

ተቃዋሚዎች በታላቁ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት አብረው ማዘናቸውን የገለጸው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ የአገሪቱን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለማጠናከር በሚያግባቡ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተለይ ደግሞ መጪውን የአካባቢና የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ በተመለከተ ሒደቱ ነፃና ፍትሐዊ ይሆን ዘንድ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመመካከር ዝግጁ መሆኑን ኢሕአዴግ የገለጸ ሲሆን፣ “በጋራ ምክር ቤቱ” አማካይነት ማለቱ ግን ተቃዋሚዎችን አላስደሰተም፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ኢሕአዴግ ያቀረበውን የመነጋገርና የመተባበር ጥሪ በተለይ ተነሳሽነት መውሰዱን አድንቀው፣ ላለፉት 21 ዓመታት ሲታገሉለት የነበረና የሚጠብቁት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውም ጭምር መሆኑን ገልጸው፣ ኢሕአዴግ እንደተለመደው ሰጪና ከልካይ የሚያደርጉ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዳያስቀምጥ ግን ይጠይቃሉ፡፡

ሥልጣን ከሕዝብ የሚመነጭ መሆኑን የሚያምኑት አቶ ሙሼ፣ ከኢሕአዴግ ጋር መነጋገር የሚፈልጉት ሥልጣን ለመጋራት ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ መሆኑን በዋናነት ይገልጻሉ፡፡ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት የሚፈጠሩበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ ፖለቲካዊ ምኅዳሩ የሚሰፋበት፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ የሚከበሩበትና ሕዝቡ ያለምንም ተፅዕኖ ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሚያደርግበት ምርጫ እንዲካሄድ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች በሚመቻችበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር ፓርቲያቸው ይፈልጋል፡፡

ተመሳሳይ አቋም ያላቸው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፣ ከኢሕአዴግ ጋር መነጋገርና መደራደር በአገሪቱ ውስጥ አለ የሚሉት ቂምና ቁርሾ ቀርቶ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበት ሁኔታ ለማመቻቸት ይረዳል ይላሉ፡፡

የመድረክ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ግን፣ ኢሕአዴግ ያደረገው ጥሪ “በጋራ ምክር ቤት” አማካይነት በመሆኑ፣ ከበፊቱ ያልተለየና ምንም አዲስ ነገር አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በምርጫ 2002 ዋዜማ የምርጫ ሥነ ምግባር ሰነድን በመፈረምና ባለመፈረም ከኢሕአዴግ ጋር አተካራ ውስጥ መገባቱን ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ የተመሠረተው የጋራ ምክር ቤት አባል ያልሆነው መድረክ፣ ሰነዱ ሕግ ሆኖ በመውጣቱ መፈረምና አለመፈረም ምንም ትርጉም ያልነበረው መሆኑን ዶክተር ነጋሶ ያስረዳሉ፡፡ አሁንም በጋራ ምክር ቤት የሚቀርበው ጥሪ ፓርቲያቸውን እንደማይመለከትና ለዓለም አቀፍ ማኀበረሰቡ ለማስመሰያ ያህል መሆኑን ይናገራሉ፡፡ “በመግለጫው ኢሕአዴግ ገደብ ጥሏል፤ በእኛ በኩል ተቀባይነት የለውም፤ አስመሳይ መግለጫ ነው፤” ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ያቀረበው የእንነጋገር ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን በመጠቆም፡፡

መግለጫው “የጋራ ምክር ቤት” በሚል  እንዳይወሰን የሚጠይቀው ግን የምክር ቤቴ አባል ያልሆነው መድረክ ብቻ አይደለም፡፡ ኢዴፓና ኢራፓም መድረኩ ሁሉም በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚካተቱበት እንዲሆን ይጠይቃሉ፡፡ በተጨማሪም ሁለቱም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ከዚህ በፊት በምርጫ 2002 ማንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ንግግር ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ እስካሁን ተግባራዊ አለመሆኑ እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ፡፡ “ቃልና ተግባር ምን ያህል ይጣጣማሉ?” ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ፓርቲዎቹ የተደረገው ጥሪ በተግባር የሚታይ እንዲሆንም ይጠይቃሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር