የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች መንግስት በዞኑ የምፈጸመውን የሰብኣዊ መብት ረገጣ፡ እስር እና እንግልት እንዲያቆም ጠየቁ፤ በመንግስት ላይ ህዝብን በማነሳሳት በምል የታሰሩ ግለሰቦች ያለ ምንም ቅድሜ ሁኔታ እንዲፈቱ ኣሳሰቡ።


የወራንቻ ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ ሪፖርተሮች ተዘዋውረው ያኗገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ መንግስት በሰበብ ኣስባቡ የተለየ ኣመለካከት እና ኣስተሳሰብ የምያራምድ ግለሰቦችን በኣስፈለገው ጊዜ እና ወቅት የተለያዩ ስሞችን በመስጠት በማስር ላይ ነው።

በሃዋሳ ከተማ ሌዊ ሆቴል ሲዝናኑ ያገኘናቸው ካላ ጌታሁን ሳርምሶ የተባሉ በከተማዋ የኣዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እንደተናገሩት፤ መንግስት በተለያዩ ጊዚያት በተለይ ከክልሉ ባለስልጣናት ፖለቲካዊ ኣመለካት የተለየ ያለ ኣመለካከት ያላቸውን ግለሰቦች ማሰሩ የተለመደ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው በኣሁኑ ጊዜ በተለይ ከሲዳማ የፊቼ በዓል ማግስት ጀምሮ በርካታ ሰዎች ህዝብን በመንግስት ላይ በማነሳሳት ተከሰው ታስረዋል።

ግለሰቦች የመሰላቸውን ፖለቲካዊ ሆነ ማህባራዊ ኣመለካከትን ያለ ምንም ገደብ እንዲያራምዱ በምፈቅድ ህገ መንግስት ባለባት ኣገር ግለሰቦች የተለየ ኣመለካከት ስላላቸው ብቻ ስብኣዊ መብታቸው መጣሱ ኣግባብነት የለውም ብለዋል።

ወጣት ንቆዲሞስ ኣየለ የተባለ በሃዋሳ ከተማ የባጃጂ ታክሲ ሽፌር በበኩሉ፤ የሲዳማ ክልል ይገባኛል ጥያቄ በተመለከተ ህዝባዊ ንቅናቄ  ከተጀመረ ወዲህ በተለይ ወጣቶች  በመንግስት የጸጥታ ሰዎች ማስፈራሪያ እንደምደርሳቸው ገልጿ፤ ለህዝቡ ጥያቄ ኣግባብነት ያለውን ምላሽ መስጠት እንጂ ሰዎችን ማስር እና ማንገላት መፍትሄ ኣይደለም ብለዋል።
ካላ ዘርሁን ናራሞ የተባሉ በተለምዶ ስሙ ሊዝ ሰፈር በምባለው ኣከባቢ መንገድ ላይ ሲጓዙ ያገኘናቸው የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃዋሳ ከተማ ብሎም በሲዳማ ዞን ወረዳዎች ውስጥ ግለሰቦች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ከመኖሪያ ቦታቸው እና ከስራ ገበታቸው እየተያዙ እንደምታሰሩ ጠቅሰው፤ ግለሰቦች በተጠረጠሩት ጉዳይ ላይ በቂ ማስረጃ ሳይቀርብባቸው በእስር እንዲቆዩ እንደምደረጉ ተናግረዋል።

ለኣብነትም በሃዋሳ ከተማ በቅርቡ የታሰሩትን ከሃያ ኣምስት በላይ ግለሰቦችን ሰም በመጥራት ግለሰቦቹ የዋስ መብት እንኳን ተከልክለው ታስረው እንደምገኙ ገልጸው፤ ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትር የኣቶ መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ ነገሮች የቀዘቀዙ ቢመስሉም በርካታ ግለሰቦች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየታደኑ መሆኑን ኣጋልጠዋል።

ከይርጋለም ከተማ ወደ ዲላ ለመሄድ ሚኒባስ ተሳፍረው ያገኘናቸው ካላ ሽብሹ ባሻ የተባሉ በይርጋለም ከተማ በተለምዶ ስሙ ኣራዳ ተብሎ ከምጠራው ሰፈር ነዋሪ በበኩላቸው፤ በይርጋለም ከተማ ብሎም በዳሌ ወረዳ ከሲዳማ ክልል ይገባኛል ጥያቄ  ጋር በተያያዘ ሰዎች መታሰራቸውን ጠቅሶ ያልታሰሩት እና ጥያቄውን በተመለከት ጠንካራ ኣቋም ያላቸው ግለሰዎችም ብሆኑ ኣቋማቸውን እንዲቀይሩ መንግስት ግፊት እያደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ኣክለውም የወረዳዋ እና  የከተማዋ ወጣቶች መንግስት የሲዳማን የክልል ጥያቄ ያለምንም ቅድሜ ሁኔታ እንዲመለስ የሚፈልጉ ብሆንም መንግስት እያደረገባቸው ባለው ጫና የተነሳ ኣቋማቸውን ኣውጥተው ለመግለጽ መቸገራቸውን ጠቁመዋል።

ኣለታ ወንዶ ከተማ ሽይ ቡና ሲሉ ያገኘናቸው መለሰ ኪሞ እና ዘለኣለም ላታሞ የተባሉ ተማሪዎች በበኩላቸው የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ መጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብቱ መሆኑን ገልጸው፤ ኣንዳንድ ባለስልጣናት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የህዝቡ ጥያቄ ለማፈን በመንቀሳቀ ላይ ናቸው ብለዋል።

የክልልም ሆነ የዞኑ ባለስልጣናት የመረጣቸውን ህዝብ ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ለግል ጥቅማቸው ማደራቸው ብሎም በኣንድ ግለሰብ ተጽዕኖ  ስር ወድቀው የግለሰቡን ፍላጎት ለማሳካት መሯሯጧቸው እንዳዛዘናቸው ተናግረዋል።
ኣክለውም መንግስት እራሱ ያረቀቀውን ህገ መንግስት በመናድ የግለሰቦችን ሰብኣዊ መብት ከመጣስ እንድቆጠብ እና ያሰራቸውን ግለሰቦች እንድፈታ ብሎም የሲዳማ  ህዝብ ጥያቄ በኣግባቡ እንድመልስ ጥር ኣቅርበዋል። 


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር