በአንዳንድ የሲዳማ ወረዳዎች በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መታሠራቸውና ቀጥለው ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እነሽፈራው ሊፈጽሙ ያሉት ክህደትና በህዝባችን በኩል መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች


የዚህ መልዕክት በጣም አጭር የሆነው ክፍል ከጉዳዩ አንገብጋቢነትና አጣዳፊነት አንጻር አስቀድሞ በጣም ባጠረ መልክ በ2 ገጽ ተለቋል፡፡ ነገር ግን 2ቱ ገጽ የተፈለገውን መልዕክት አሟልቶ ማስተላለፍ ስለማይችል ይህ ጽሁፍ እንዲዳረስ ለማድረግ ተወስኗል፡፡
የተከበራችሁ አባቶቻችን (ሽማግሌዎች)፣ የተወደዳችሁ ተማሪዎች፣ የተከበራችሁ ነጋዴዎችና አርሶአደሮች፣ ውድ ምሁራን አሁን ያለንበት ወቅት ከምን ጊዜውም በላይ ፈታኝ መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ ያለነው ከምን ጊዜውም በላይ መብታችን ተረግጦ፣ ህገ-መንግሥታዊ ጥያቄያችንንና ክልል ለመሆን ያስተላለፍነው ውሳኔያችንን ተከልክለን ባለንበት ሁኔታ ነው፡፡ የህዝብ ቁጣ ተባብሶ ባለበት ሁኔታ አሁንም የባሰ ክህደት ሊፈጽሙ እየሠሩ መሆኑ ስለተደረሰበት ይሄንን መልዕክት ማስተላለፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ እነሽፈራው ከየወረዳው ሁሉም ቀበሌዎች ቢቻል የራሱ ዘመድ የሆኑና ታማኝ የሆኑ ሽማግሌዎችን ካልተቻለም የዋህ የሆኑና ለማታለል የሚመቹ ሰዎችን ወደ ሐዋሳ ጠርተዋል፡፡ ዋና የማደናገሪያ አጀንዳቸው፡ -
  1. የህዝብ ጥያቄው ተመልሷል፡፡ በከተማው በሁሉም የሹመት ቦታዎች የሲዳማ ተወላጆች ተሹመውበታል፡፡ የክልል ጥያቄ ለማንሳት ግን አሁን ጊዜው አይደለም አይጠቅመንም፡፡ ስለዚህ ተውት የሚል ነው፡፡
እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ይሄንን ሴራ የጠነሰሱት ከሁሉም ቀበሌያት ያን ሁሉ አመራርና የተገኘ ሽማግሌ ሁሉ ጠርተው ሲዳማን የሚወክል ሰፊ ህዝብ የተስማማ ለማስመሰል የተለያዩ የዜና አውታሮችን (የመገናኛ ብዙሃንን) ጠርተው የተለመደውን ውሸታቸውን ሊያስተጋቡ ተዘጋጅተው ነው፡፡ እዚህ ጋ ልብ ልንል የሚገባው ተሰብሳቢዎች የተናገሩት ሳይሆን የሚተላለፈው በዋናነት የውሸትና የማስመሰል ድራማ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
ነገር ግን ሁላችንም እንደምናውቀው የህዝባችን ጥያቄ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሹመት ቦታዎች ጥያቄ አይደለም፡፡ ይህማ እነሽፈራው ከቤታችን ገብተው ሊዘርፉን ሲሞክሩ ከሰበሰቡ በኋላ እንደማያዋጣ በማወቅ መልሰው እንደተውት ንብረታችን የሚቆጠር ነው፡፡ ቀድሞውንም የማንም ሳይሆን የእኛው መብት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ የሚታለል ማን ሞኝ አለ፡፡ ስለዚህ ጥያቄያችን ክልል የመሆን ጥያቄ መሆኑን እንደገና ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ ሽፈራው በተደጋጋሚ ባስተላለፈው መልዕክት በሲዳማ ሬዲዮና በደቡብ ኤፍኤም “በሐዋሳ የሚኖረው ሲዳማ ያልሆነው ህዝብ ቁጥር ከሲዳማ በእጅጉ የሚበልጥ ስለሆነ ስልጣን እንከፋፈል ማለታችን አግባብ ቢሆንም ለጊዜው ትተናል፤ ክልል ለመሆን ጊዜው አይደለም፤ ሲዳማ ክልል ቢሆን ዛሬ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ባለሙያዎች የት ይገባሉ? ደቡብ ኦሞ ሄደው እየተሠራ ባለው የስኳር ፋብርካ መቀጠር አይችሉም፤ ክልል መሆን ለሲዳማ ምንም ጥቅም የለውም፤ ይልቅ ሌላ የበለጠ ጥቅም ይቀርበታል…ወዘተ” በማለት የአላዋቂነት ደረጃውን በእጅጉ በሚያሳብቅ መልኩ ሲለፈልፍ ተስተውሏል፡፡ አባባሉን እንደወትሮው ብልጠት ነው ልንል አንችልም፡፡ ብልጥ ወይም ጥበበኛ ሰው (ውስጡ ተንኮል ካለበት) የሚከተለው መንገድ ሌላውን ሊያሳምን የሚችልና ትንሽ እንኳ ቢሆን እውነት የሚመስሉ ንግግሮች ውስጡ ያሉበትን ፒሮፓጋንዳ ነው የሚያስተላልፈው፡፡ ይህ ሰው ለተቀመጠበት ቦታ የማይመጥን፣ የሚለውን የማያውቅ፣ ለማን እያወራ እንደሆነ የማያውቅ፣ የሚለው ያለቀበት፣ የሚመራበት ዓላማና እሴት የለሌው፣ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ለመገመት የማይመች አላወቂ መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ለሲዳማ ህዝብ የትግሬ፣ የአማራ፣ የኦሮሞና መሰል ክልል ተመራቂዎች የት ነው የሚቀጠሩት የነበረው ብሎ የሚገመግም ሰው የለውም ብሎ ያምናል? ሽፈራው፡፡ ትላልቆቹን ክልሎች እንተው ከተባለም የአፋር፣ የቤንሻንጉል፣ የሀረሪ፣ የጋንቤላና መሰል ክልሎች ተወላጆችስ የት ነው የሚመደቡት? ከነዚህና መሠል ክልሎች መጥቶ ሲዳማ ውስጥም ሆነ ደቡብ ውስጥ የሚሠራ ሰው የለም? በርግጥ ሞልቷል፡፡ በደቡብ ኦሞ ስኳር ፋብርካው ፕሮጀክቶች ውስጥ በአሁን ጊዜ ሌላው ኢትዮጵያዊ አይሠራም? ለመሆኑ ማስታወቂያ ሲወጣ “ከዚህ ክልል ብቻ የመጣ ወይም ተወላጅ” ተብሎ ሲወጣ አይተህ ታውቃለህ ሽፈራው ወይስ ይሄንንም አታውቅም? እውነት ነው አታውቅም ማለት ነው፡፡ ሌላ እውነታ እናንሳ ለመሆኑ እስከአሁን በደቡብ ክልል የሲዳማ ተወላጆች ተቀጥረው የሚሰሩበት የት ነው ከሲዳማ ውጭ? አሁንኮ እየተባለ ያለው እንኳንስ ሌላ የክልሉ አከባቢዎች ሄዶ ሊሠራ ያለበትም በዝቶብሀል ስለዝህ የሙያ መደቦችን ሳይሆን የሃላፊነት ቦታዎችን አካፍል ነው እየተባለ ያለው፡፡ የት ክልል ነው ይህ ተብሎ የምያውቀው? በርግጥ ሲዳማ ዞን አሁንም ሆነ ለወደፊቱ ክልል ሲሆን ባለሙያዎች ከየትም መጥተው ይሠራሉ እየሠሩም ናቸው፡፡ በርግጥ እውነት ነው ሲዳማ ክልል ከሆነ ለአንተ አይጠቅምም፡፡ መደበቂያ ታጣለህ፡፡ እንደአሁኑ እያታለልክ መኖር አትችልም፡፡ አንተ ግን ብቻህን ሲዳማ አይደለህም፡፡ ስለዚህ ሲዳማ ማለት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ማለት ስለሆነ እውነቱን አውራ እግዝአብሔርንና የእግዝአብሔርን ህዝብ ከዚህ በላይ አታሳዝን፡፡
በጣም የገረመን ሽፈራው በሐዋሳ ያለው ሌላው ህዝብ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ የስልጣን ክፍፍል እናድርግ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የተገረምነው 1) ሽፈራው የሲዳማ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ከተማ ይግቡ የሚል አጀንዳ ህጋዊነት ባለው መልኩ ተቀባይነት ሲያገኝ ዘመዶቹ፣ ወዳጆቹና አጫፋሪዎቹ ቢያንስ ከ3 ጀምሮ እስከ 15 እና 20 ቦታዎች እንዲወስዱ በማድረግ ቦታ ሲያስቸበችብ ቆየ፤ 2)ሥርዓቱ የተዋቀረውና የተገነባው በብሔር ብሄረሰብ መብትና ራስን በራስ በማስተዳደር መብት ላይ መሆኑን ዘነጋው እንዴ? አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብለህ ስትሰብከን የነበረው ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ ተቀየረ እንዴ? የግለሰቦች መብት ነው የቡድን ቅድሚያ የሚሰጠው በኢህአዴግ መሥመር? ከዚህ አንጻር የትኛው ህዝብ ነው ቢያንስ የዞንና የወረዳ አስተዳደር ከለሌበት ወደ ሀዋሳ የመጣው? እንዳውም በክልል ደረጃ ሳይቀር ከተደራጁ ወገኖች የመጡ ነዋሪዎች መኖራቸውን ማስተማር ያለብን አይመስለንም፡፡ ይሄንንስ አጀንዳ ይዛችሁ ወደ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሻሸመኔና ሌሎች አከባቢዎች (ከተማዎች) የምትገቡት መቼ ነው? መቼም እናንተ ባትሆኑም ጌቶቻችሁ ይሄ አጀንዳ ይኖራቸዋል፡፡ ጌቶቻችሁን ከሰሟችሁ “ይሄንን ውንብድና ከመተግበራችሁ በፊት ህገ-መንግሥቱን ቀይሩ…” በሏቸው፡፡
  1. በጣም የሚያሳዝነው የታቀደልን ዋናውና እውነተኛው የዚህኛው ስብሰባ ዓላማ የኃይለማሪያም ደሳለኝን አጀንዳ መፈጸም ነው፡፡ ሚሊዮን ማቴዎስ በጋዜጣው ላይ በገባው ቃል-ኪዳም መሠረት የወላይታ ተወላጅ ሽማግሌዎች የሆኑ ሰዎችን እንደጠሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከእነርሱ ፊት ቀርቦ የሲዳማ ሽማግሌዎች በሲዳማ ስም እነርሱን ይቅርታ እንዲጠይቁ ለማድረግም እንደሆነ ታውቋል፡፡
ለህዝባችን ለማስተላለፍ የምንፈልገው መልዕክት የሲዳማ ህዝብ ከየትኛውም ህዝብ ጋር አልተጋጨም፤ ስለዚህም ምንም ይቅርታ መጠየቅ አይጠበቅበትም የሚል ነው፡፡ ለህዝባችን ከሌላው ወገን ህዝብ ጋር አብሮ እንዴት በሠላም መኖር እንዳለበት መምከርም ሆነ በህዝብ ለህዝብ ኮንፎራንሶች ይቅርና አንድ ኮንፎራንስ ለማካሄድ ማሰብ በራሱ “ልጅ እናቷን ምጥ አስተማረች” እንዲሉ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ቢቀርባችሁ ጥሩ ነው ህዝባችን ከሌላው ህዝብ ጋር ምንም ቅራኔና ቁርሾ የለበትምና፡፡
ውድ የሲዳማ ህዝብ ሆይ በአሁን ጊዜ እነሽፈራው በተለያዩ ወረዳዎች ህዝባችንን እያሠሩትና እያዋከቡት ነው፡፡ በዚህች ሰዓት፡ -
  1. በጭሬ ወረዳ 7 መሀንዲሶች፣ 2 የጋዜጠኝነት ሙያ ተማሪዎች 12 ሌሎች ሙያዎችን የተማሩና እየተማሩ ያሉ በድምሩ 21 የዩንቨርሲቲ ተመራቂዎችና ተማሪዎች ታስረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ አሰቃቂ ድብደባና እንግልት እየደረሰባቸው ይገኛሉ፡፡ የስም ዝርዝራቸውም፡ -

  1. ተፈራ ቄንፋቶ
  2. ብሪሃኑ ዳና
  3. ሀጎሳ ሀንፈቃ
  4. ብዙነህ ጸጋዬ
  5. ወገኔ ተሊላ
  6. ብሪሃኑ ሌዳሞ
  7. ሲሳይ ደሴ
  8. ደሳለኝ ደበሳ
  9. ፍቅረ ስሪቃ
  10. ዘለቀ ኦቶ
  11. ሹምቡሎ ሹታ
  12. ታፈሰ ደበበ
  13. ፉላሳ ፉልቃ
  14. ዘውዴ ሳንባቶ
  15. ታምሩ ለካ
  16. ዳጎሌ ቁጣሻ
  17. በቀለ ባናታ
  18. ከበደ ተፈራ
  19. ዶራ ላዴጎ
  20. ወራቆ ዶማራ
  1. ወረዳው መንገድ እንዳልነበረ የሆነበትና በእንስሳት ጀርባ ለመሄድ እንኳ የማይመችበትና የመገናኛ ብዙሃኖች ያልተሟሉበት የሚገኝ በመሆኑ ታሳሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ ታውቋል፡፡ ስለዚህ የሲዳማ ህዝብ ይሄንን በማወቅ ወጣት ሽማግሌ ሳይል ሁሉም በአንድ ድምጽ እነዚህ ለመብታቸውና ለመብታችን እየታገሉ የታሰሩ ካለምንም ቅድመሁኔታ እንዲፈቱና ጥያቄው በአስቸኳይ እንዲመለስ እንዲያደርግ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡
  2. ሌላው በአሁኑ ሰዓት እንደትልቅ ጥበብ ይዘው እየሠሩበት ያለው አካሄድ በወጣቱ ተቀባይነት ይኖራቸዋል ተብለው የሚታመኑ የወጣቱ ጓደኛ የነበሩ ወጣቶችን በመሾም እነዚህ አዲስ ወጣት አመራሮች የክልል ጥያቄውን አንግበው ህዝብ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችን በጓደኝነትና በጥቅም ይዘው እንዲያዘናጉ፣ እንዲያረሳሱና ጥያቄው እንዲዳከም ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ፣ ከተቻለም በተቃራኒው እንደራሳቸው ካድሬ አድርገው እንዲጠቀሙ ታቅዶ ተሠማርተው እየሠሩ ያሉ መሆናቸው ተደርሶበታል፡፡ እነዚህ አዲስ አመራር ወገኖች መጀመሪያ ለሲዳማ የክልል ጥየቄ አይመለስም የሚለውን ሀሳብ እንዲያምኑ የተደረጉ ናቸው፡፡ ለዚህም ማባበያና አፍ ማስያዣ ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቦ መምጣቱ ተደርሶበታል፡፡ ምንም እንኳ ወጣቱ በዚህ ተታሎ መብቱን ይሸጣል ተብሎ ባይጠበቅም በራሱ በወጣቱ፣ በምሁሩ፣ በሽማግሌውና በሁሉም በህ/ሰቡ ትኩረት ተሰትጥቶና በአንክሮ ሊመከርና ውድቅ ሊደረግ የሚገባ አደገኛ አካሄድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል እንላለን፡፡ በመቀጠልም ክልል ሰው የሚሰጠንና የሚነሳን ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥትም ሆነ መስመር የሚሰጠንና የሚከለክለን ዳቦ አይደለም፡፡ ክልል የመሆን መብት ህገ-መንግሥቱ የሰጠንና እኛም የወሰነው መሠረታዊ መብት ነው፡፡ ካልተከበረም የትኛውንም ዋጋ ከፍለን የምናስከብረው ዋናው የመኖር ያለመኖር ህልውናችን ነው፡፡ ቤቱ ተወስዶበት ወይም በመሬቱ ላይ በሀገሬው ህግ መሠረት ቤት ለመቀለስና ለመሥራት ፈልጎ ተከልክሎ እሽ ብሎ ትቶ የሚቀመጥ ማነው? ይሄንን የሚቃወም አካሄድ ከየትም ይምጣ መንግሥትን ጨምሮ ኢህገ-መንግሥታዊ አካሄድ ነው፡፡ ለህገ-መንግሥት መገዛት ያለበት ህዝብ ብቻም አይደለም መንግሥትና መስመርም ነው፡፡ ይህ ህግ ከየትኛውም ህግና መስመር የበላይ ህግ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ሲዳማ ክልል ሆነናል፡፡ የቀረው እውቅና የማግኘት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ነው እየታገልን ያለነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ማባበያ ልንታለል እንደማይገባ መረዳት አለብን፡፡
  3. ካድሬዎቻቸውንና አመራሮቻቸውን ከየወረዳው ጠርተው “አቅመቢሶች ናችሁ፣ ዝም ብላችሁ የአልፋን ወረቀት ብቻ ተሸክማችሁ ነው የምትዞሩት እንጂ የምታውቁት ነገር የለም፣ አቅም የላችሁም፣ ማስፈጸም አልቻላችሁም…” ብለው ሲሳደቡ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለነገሩ የሚቃወማቸው ዓይነት ካድሬ በተቻለ መጠን ቀድሞውንም የማይሰበስቡና የሚሾመውም የሽፈራውና የሚሊዮን ዘመድ፣ በአምቻ በጋብቻ የተሳሰረ፣ ካልሆነም ጎሳቸው የሆነ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ቢሳደቡ አይደንቅም፡፡ አሁንም ተሾሙ የተባሉ በሙሉ ማለት ይቻላል በዚሁ መመዘኛ የገቡ ናቸው፡፡ ታዲያ ሁሉም አመራሮች ተባብረው ይሄንን ሂደት ሊቃወሙና ሊያስቆሙ ይገባል እንላለን፡፡
  4. ጥሩ ሲዳምኛ ተናጋሪ የሆኑና ሲዳማ ውስጥ አድገው የህዝቡን ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ ነባር የደህንነት ሰዎች ከያሉበት ከሀገሪቷ የተለያዩ አከባቢዎች ተጠራርተው ሲዳማ ከተዋል፡፡ ሀዋሳን ጨምሮ ሁሉም የዞኗ ከተሞች በነዚህ ወገኖች ተጨናንቀዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ሙሉ በሙሉ የህዝባችን ጠላቶች ናቸው ብለን ባናምንም ግን ቁጥራቸው የማይናቅ ሰላዮች ግን ጡቱን ጠብተው ያደጉበትን ህዝብ እየበሉትና አሳልፈው ለጠላት እየሰጡት ነው፡፡ የእናት ጡት ነካሾች፡፡ በርግጥ ከፍሎቹ ይሄንን እውነታ አያጡም ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ ባንሸማቀቅና ባንፈራቸውም መጠንቀቅ ጥሩ ነው እንላለን፡፡
  5. የአቋም አቅጣጫችን
  1. ጥያቄያችን ክልል የመሆን ጥያቄ ብቻ መሆኑንና ከዚህም አጀንዳ ውጭ የትኛውንም የማስመሰልና የማሞኛ አጀንዳ አንስተን መነጋገር የለብንም፡፡ አሁንም አቋማችን አንድ ነው፡፡ ጥያቄያችን እስከሚከበር ድረስም በርትተን እንሠራለን፡፡
  2. ልጆቻችን የታሰሩት ህገ-መንግሥታዊ መሠረት ያለው ጥያቄዎቻችንን አንስተው ስለሆነ ከዚህ ቀደም በገባነው ቃል መሠረት (አብሮን የሚታገል ማንኛውም ሰው ሲታሰር እስከሚፈታ ቀጣይነት ያለው ጥያቄ ማቅረብና እስከመጨረሻው ከጎኑ/ኗ መቆም በሚለው ኪዳናችን መሠረት) በአስቸኳይ እንዲወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋል፡፡ ከዚህ አንጻር የሲዳማ ህዝብ ወጣት ሽማግሌ ሳይል ሁሉም በአንድ ድምጽ እነዚህ ወገኖች ካለምንም ቅድመሁኔታ እንዲፈቱና ጥያቄው በአስቸኳይ እንዲመለስ ባገኘው አጋጣሚና መንገድ ሁሉ ጫና እንዲፈጥር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
  3. እነሽፈራው ከዚህ በኋላ የሚታመኑበት ምክንያትና ሁኔታ የለም፡፡ እነርሱን ፍለጋ ህዝባችን ሓዋሳ የሚመጣበት ምክንያት የለም፡፡ ሊያነጋግሩት ከፈለጉ ያለበት መሄድ አለባቸው፡፡ ስለዚህ አንድም ተሰብሳቢ ወደሐዋሳ መምጣት የለበትም፡፡
  4. ስብሰባ የትም ይደረግ የት ዋናው አጀንዳችን ሁሌም “የክልል ውሳኔው ተግባራዊነቱ ለምን ዘገየ?” የሚል ብቻ መሆን እንዳለበት ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ ከዚህ ሌላ የመነጋገሪያ አጀንዳ ለንም፡፡
  5. ከማንም ጋር ስላልተጣላን ይቅርታ የምንጠይቀውም ሆነ ስለዚህ ጉዳይ የምንነጋገረው አካል የለም፡፡ ስለዚህ ማንም ሲዳማን እወክላለሁኝ የሚል ይሄንን ስህተት እንዳይሠራ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ይልቅ በመንግሥት፣ በእነኃይለማሪያምና በነሽፈራው ይቅርታ መጠየቅ ያለበት የሲዳማ ህዝብ መሆኑ ሊሠመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
  1. ማሳሰቢያ 2- ከላይ የተገለጸው ሴራ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ሰነድ ኮፒ የደረሰው ማንም የብሔሩ ተወላጅ በዛሬው ቀን 5 ኮፒ በማድረግ ይሄንን ሴራ ለመቀልበስ የሚደረግ ትግል እንዲደግፍ እንጠይቃለን፡፡ የሰነዱ መልዕክት ላልገባቸው በቡድን እየተነጋገሩና እየተመካከሩ የጋራ ግንዛቤ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ ለሚገኙ የብሔሩ ዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች በትክክል እንዲደረሳቸውና በአከባቢያቸው በቂ ግንዘቤ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል እንላለን፡፡
  2. ሐምሌ 23/2004

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር