የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስክሬን ከሰዓታት በኋላ አዲስ አበባ ይገባል፤ በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሀላ እስኪፈፅሙ ድረስ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስራ በተጠባባቂነት ተረክበው ይሰራሉ ተባለ


አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 15፣ 2004 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስክሬን ከሰዓታት በኋላ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ  እየተጠበቀ ነው ። 

በአሁኑ ወቅትም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስትሩን  አስክሬን በክብር ለመቀበል በቦሌ  አውሮፕላን ማረፊያ  አከባቢ  እየተሰባሰቡ ይገኛሉ።


የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትናንት ማምሻውን በህክምና ሲረዱ በነበሩበት  ሆስፒታል ማረፋቸውን  ነው ያስታወቀው ። 

ምክር ቤቱ በመግለጫው ኢትዮጵያን ላለፉት 21 ዓመታት በከፍተኛ ብስለትና ብቃት ሲመሩ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስው ዜናዊ ካደረባቸው ህመም ለመፈወስ በውጭ አገር በህክምና ሲረዱ መቆየታቸውን ጠቅሷል ።

ላለፉት ሁለት ወራት በህክምና ሲረዱና በጤናቸውም ላይ መሻሻል ሲታይ ከቆየ በኋላ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ  በተከሰተ ደንገተኛ  ኢንፌክሽን ህመማቸው አንደገና ተባብሶ ለአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል  ገብተው ነበር ።

በህክምና ሙያተኞች ከፍተኛ እገዛ ቢደረግላቸውም በትናንትናት እለት ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ40 ላይ በድንገት ማረፋቸውን ምክር ቤቱ ለአገራችን ህዝቦች በታላቅ ሀዘን ገልጿል ።

ኢትዮጵያንና  ህዝቦቿን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነትና በታማኝነት አገራቸውን  አገልግለው ከፍተኛ የለውጥ ተስፋ ያሳዩን  መሪ እንደነበሩ  ነው ምክር ቤቱ የገለፀው  ።

አቶ መለስ ኢትዮጵያ በልማታዊ ዲሞክራሲያዊ አቅጣጫ እንድትጓዝ ጥራት ያላቸው ፖሊሲዎችንና  ስትራቴጂዎችን  ነድፈው በብቁ አመራራቸው በገነቧቸው ድርጅቶችና መንግሰት አማካይነት ተግባራዊ ማድረግ የቻሉና በአገራችን  በመካሄድ ላይ ያለው ታላቅ አገራዊ የህዳሴ ጉዞ በሰመረ አቅጣጫ እንዲጓዝ ያደረጉ ታላቅ መሪ እንደነበሩ  ምክር ቤቱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል ።
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እረፍት ተከትሎም በአገሪቱ ብሔራዊ የሀዘን ቀን ታወጇል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን እረፍት ምክንያት በማድረግ የመንግሰት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ፥ የቀብራቸውን ስነ ስርዓት በተመለከተም መቼና እንዴት እንደሚፈፀም የሚያስተባብር ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚቴም መዋቀሩን ገልፀዋል።
በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሀላ እስኪፈፅሙ ድረስ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስራ በተጠባባቂነት ተረክበው እንደሚሰሩ ተመልክቷል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር