የደቡብ ክልል የሚገኙ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማቸውን መሪር ሀዘን ገለፁ

 አዋሳ ነሐሴ 17/2004 በደቡብ ክልል የሚገኙ የተለያዩ መስሪያ ቤቶችና ተቋማት አመራር አባላትና ሰራተኞች በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማቸዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለጹ ነዉ ።
የደቡብ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ፣የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ፣የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምና የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ሠራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች በታላቁ መሪያችን ሞት ጥልቅና መሪር ሀዘን ተሰምቶናል ብለዋል ።
ቢሮዎቹና ተቋማቱ ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ ላይ እንዳስታወቁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከወጣትነት እድሜያቸዉ ጀምሮ እስከ እለተ ሞታቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት ተላቆ በእድገትና ብልጽግና ጎዳና እንዲጓዝ ታላቅ ራእይ ሰንቀዉ የተነሱ ቆራጥና አስተዋይ መሪ ነበሩ ብለዋል ።
የየቢሮዎችና የተቋማቱ ሰራተኞች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የአመራር ጥበባቸውን በመጠቀም ኢትዮጵያን በልማት ለማሳደግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አሁን ለደረሰንበት የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ስርዓት ያበቁ ታታሪና ብልህ መሪ እንደነበሩ አስታዉቀዋል ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ "ለመጪው ትውልድ ዕድገት፣ ብልፅግናና ልማትን እንጂ ድህነትን አናወርስም "በማለት በቆራጥነትና በታላቅ ኃላፊነት መንፈስ ሲሰሩ የቆዩ የለውጥ ሐዋሪያ ናቸው ሲሉ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ገልፀዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኢትዮጵያ በአለም ከምትታወቅበት የተመፅዋችነትና የረሃብ ታሪክ እንድትላቀቅ በዓለም ትልቅ የልማት ተስፋ ሆነው ከሚታዩ የዓለም አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደረጉ ጀግናና በሳል መሪ ነበሩ ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የእርሳቸዉን በጎ ተግባር በመከተል ብቃት ያለው የልማት ሠራዊት መሆን የሚችል በሁሉም መስክ የሰለጠነ የሰው ኃይል በብዛትና በጥራት በማፍራት የድርሻውን እንደሚወጣም አስታውቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ሠራተኞች በበኩላቸዉ በታላቁ መሪያችን ድንገተኛ ሞት ብንጎዳም እርሳቸው በቀየሱት የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት የተገገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል በእርሳቸዉ ስራ እንድንኮራና እንድጽናና እንሆናል ብለዋል ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን የአፍርካ ህዝቦች ታላቅ ተስፋ የነበሩ በዓለም አቀፍ ደረጃም ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ብልህና አርቆ አስተዋይ የአፍርካ መሪ ነበር ሲሉ የክልሉ ሲቨል ሰርቪስ ቢሮ አመራርና ሠራተኞች አስታዉቀዋል ።
እርሳቸዉ የጀመሯቸው የልማት ውጥኖች ከግብ እንዲደርሱ ጠንክረን እንሰራለን፣ አባይ ይገደባል ፣መለስ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራል በማለትለእርሳቸዉ ያለቸዉን ጽኑ ፍቅር አረጋገጥዋል ።፡
በተመሳሳይ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አመራርና ሠራተኞች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለህዝቦች ደህንነት፣ ለዜጎች እኩልነትና ለሰብአዊ መብት መጠበቅ እንዲሁም ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ሌት ከቀን ሲተጉ የነበሩ ታላቅና አኩሪ መሪያችን ነበሩ ሲሉ ገልጠዋል ።
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሞት የተሰማን ሀዘን ክልክ ያለፈና መራራ ቢሆንም እሳቸው የጀመሩትን የሰላም፣ የልማትን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ማኔጅመንትና ሠራተኞች በበኩላቸዉ ባለራዕዩ መሪያችን ያስቀመጡትን የአምስት አመቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካትና የእርሳቸውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የአገራችን ህዳሴ ጉዞ ለማፋጠን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር