የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ


አዲስ አበባ ነሐሴ 15/2004 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
የሚኒትሮች ምክር ቤት ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አገራችንን ላለፉት 21 ዓመታት በከፍተኛ ብስለትና ብቃት ሲመሩ የቆዩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካደረባቸው ሕመም ለመፈወስ በውጭ አገር በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 5፡40 በድንገት ማረፋቸውን ለመላው የአገራችን ሕዝቦች በታላቅ ሐዘን ይገልጻል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላለፉት ሁለት ወራት በህክምና ሲረዱና በጤናቸው ላይ መሻሻል ሲታይ ከቆየ በኋላ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በተከሰተ ድንገተኛ ኢንፌክሽን እንደገና ሕመማቸው ተባብሶ ለአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል ገብተው በህክምና ሙያተኞቻቸውም እገዛ ቢደረግላቸውም በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 5፡40 ሲሆን ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነትና በታማኝነት አገራቸውን አገልግለው ከፍተኛ የለውጥ ተስፋ ያሳዩንን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እልፈተ ህይወት ሲገለጽ በኃዘን በተሰበረ ልብ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከምንም ነገር በላይ አገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚወዱ ለዚች አገርና ሕዝብ የላቀ ራዕይ የነበራቸው መሪ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራዕያቸውን እውን ማድረግ የጀመረና አስተማማኝ ውጤት ማምጣት የቻለ ድርጅትና መንግሥት የገነቡ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ መጠራት እንድትጀምር ያደረጉ ታላቅና እጅግ አርቆ አሳቢ መሪ ነበሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አገራችን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ እንድትጓዝ ጥራት ያላቸው ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች ነድፈው በብቁ አመራራቸው በገነቧቸው ድርጅትና መንግሥት አማካኝነት ተግባራዊ ማድረግ የቻሉና በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለው ታላቅ አገራዊ የህዳሴ ጉዞ በሰመረ አቅጣጫ እንዲጓዝ ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአገራችን ህገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፣ የህዝቦች እኩልነትና የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝተው በተግባር ላይ እንዲውሉ በአገራችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና በድህነት የሚማስኑ ወገኖችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ተግባር የፈጸሙ፣ ያደረጉ ኢትዮጵያን በአዲስና ጽኑ ዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ ያዋቀሩ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያና አፍሪካ ታላቁን የለውጥ ሃዋሪያ ልጃቸውን አጡ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ትንሳኤ ያበሰረው አዲስ የአመራር ትውልድ አርቆ አሳቢ መሪውን ተነጠቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አገራችንን በከፍተኛ ደረጃ ለመለወጥ የሚያስችለው የታላቁ የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሐንዲስ ከመሆናቸውም በላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ካደረባቸው ሕመም ጋር እየታገሉ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊነቱን የመሩና አገራቸው የጀመረችውን ተከታታይና ፈጣን ዕድገት የማስመዝገብ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያደረጉ ታላቅ የሕዝብ ልጅ ነበሩ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱና ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድና ለአፍሪካ ሠላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ፣ ኢትዮጵያ፣ ለሶማሊያ፣ ለደቡብና ሰሜን ሱዳን፣ ለሩዋንዳ ለቡሩንዲና ለላይቤሪያ ዘላቂ ሠላም ታሪክና መላ አፍሪካውያን የማይዘነጉት አስተዋጽኦ እንድታበረክት ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአፍሪካ ሕዝቦች ድምጽ እንዲሰማ አፍሪካ በንግድና በልማት፣ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር፣ በሠላምና መረጋጋት አቅጣጫ እንድትጓዝ ታላቁን የኔፓድ ፕሮግራም ከአፍሪካውያን የትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ያመነጩና ይህን የተቀደሰ ሃሳብ በአገራቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያ በእርግጥም የተለመደ አፍሪካዊ ኃላፊነቷን ከውስጧ በመጀመር እንድትወጣ ያበቁ ታላቅ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ህዳሴ መሪ ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዓለማችን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል ሥርዓት እንዲዋቀር የታዳጊ አገሮች ድምፅ በመሆን በዓለም አደባባባይ የተሟገቱና ተቀባይነት ያተረፉ ታላቅ መሪ ነበሩ። በዓላማችን የተፈጥሮ ሀብት ሚዘን እንዲጠበቅ፣ በቃላቸው መሰረት ኢትዮጵያ የአረንጓዴው ልማት ሃሳባቸው ተግባራዊ ማሳያ እንድትሆን ያደረጉ ታላቅና በሳል መሪ ነበሩ።
በብስለታቸውና በአርቆ አሳቢነታቸው በአገራችን ቦግ ብሎ የበራውን የተስፋ ሻማ የለኮሱ ኢትዮጵያንና መላውን የጥቁር ማህበረሰብ ያኮሩ ፣ መላው ዓለም ብቃታቸውን የመሰከረላቸው ታላቅ መሪ ነበሩ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ሕይወት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለማችንም አንድ አርቆ አሳቢ አዕምሮና የለውጥ ኃይል እንዳጣች በፅኑ የሃዘን መንፈስ ይገነዘባል።
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦችና የኢትዮጵያ ወዳጆች
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አለጊዜ መሞት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በአገራችን አስተማማኝ ዲሞክራሲያዊና ልማታዊ ህገ መንግስታዊ ስርዓት ገንብተው በማለፋቸው ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ይጽናናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የለውጥ ሃሳቦች ዛሬ የ80 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ሃሳቦች ሆነዋል፡፡ የልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ ጅምራቸው በመላው አፍሪካዊያን ዘንድ አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ፣ ለለውጥና ለተሻለ ሕይወት መነሳሳትን የጋበዘ ሆኗል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፖሊሲና ስተራተጂዎች መቼም ቢሆን ደከመኝ በማያውቁ የትግል አጋሮቻቸውና ድርጅታቸው እንዲሁም በልማታዊ መንግስታችንና በመላው አገራችን ህዝቦች ንቁ ተሳትፎ በከተማና በገጠርም በተግባር ተተርጉመው አገራችንን በፍጥነት ለመለወጥ የሚያስችሉ ፍቱን አቅጣጫዎች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ታላቁ መሪያችን ዛሬ ከጎናችን ቢለዩንም ትተውልን የሄዱት ህገ መንግስታዊ ልማታዊና ዲሞክራሳዊ ስርዓት ከአለት በጸና መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ በታላቁ መሪያችን ምንጊዜም ቢሆን እንድንኮራ በራሳችን ያለን መተማመን ከፍተኛ እንዲሆንና በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ህዳሴ እውን የማድረግ ጉዞ መቼም ቢሆን እንደማይቀለበስ ያረጋገጠልን ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቋን መሪዋን በማጣቷ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ብትሆንም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ብሩህ አእምሮ ያፈለቃቸው መሰረታዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች ተጠናክረው ተግባራዊ መሆን ይቀጥላሉ፡፡ በህገ መንግስታችን የተከበሩ የግልና የቡድን መብቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰፍተውና ጎልብተው እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡ በአገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፈለግና ራእይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በአፍሪካ በመጫወት ላይ ያለችው ገንቢ፣ ሰላማዊና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥል ከመሆኑም በላይ አገራችን ዛሬም እንደትናንቱ የመልካም ጉርብትና አብነት ሆና ትቀጥላለች፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ በአፍሪካ ህብረትና በዓለም አደባባይ የምትጫወተው ገንቢ ሚና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባስቀመጡት ራእይና ፈለግ በመመራት ተግባራዊነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች
ታላቁ የአገራችን መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመታመማቸው ወሬ ከተሰማ በኋላ መላ የአገራችን ህዝቦች ለመሪያቸው ልዩ ልባዊ ፍቅር በማሳየትና በየእምነታቸው መሠረት በፀሎች መልካም ምኞታቸውን ሲገልፁ እንደቆዩ በከፍተኛ አድናቆት ተገንዝቧል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መላ የአገራችን ህዝቦች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከመንግስት ጎን ተሰልፈው አገራቸውን በተረጋጋ ሰላማዊና ትክክለኛ አቅጣጫ ለማስቀጠል ላደረጉት ከፍተኛ ትግል ያለውን አድናቆት እየገለፀ ከእንግዲህም አገራችንን ከዚህ አስቸጋሪ ነገር ግን በአስተማማኝ ሁኔታ ከምናልፈው ወቅት ባሻገር ለዘላቂ እድገቷ፣ ሰላሟና የህዝብ ተጠቃሚነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እንድንቀሳቀስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በርካታ የአፍሪካና የዓለም መሪዎች የታላቁ መሪያችንን ጤንነት ሁኔታ ከሰሙ በኋላ በተለያዩ መንገዶች ለላኩንል የመልካም ምኞትና የድጋፍ መግለጫ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በከፍተኛ አድናቆት እንደሚመለከተው፤ በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ከሁሉም አገሮች ጋር የፈጠረችውን መልካም ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ለመግለጽ ይወዳል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህክምና ሲረዱ በቆዩበት ወቅት ሁሉ ከአጠገባቸው ሳይለዩ የተቻላቸውን ሁሉ ድጋፍ ላደረጉና የመሪያችንን ጤንነት ለመመለስ አቅማቸው የፈቀደውን ትብብር ላደረጉልን የህክምና ሙያተኞች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀብር ስነስርዓት የሚፈፀምበትን ሂደት በማስመልከት ቀጣይ መግለጫዎችን የሚያቀርብ ሲሆን በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሠረት ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን እየመሩ ይቀጥላሉ፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች
አገራችን ታላቁንና አርቆ አሳቢውን መሪዋን በማጣቷ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የለውጥና የአገር ግንባታ ራእይ ተግባራዊ ለማድረግ በከፍተኛ አገራዊ የአንድነት መንፈስ ልንረባረብ የምንገደድበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህ አስቸጋሪ ወቅት በአስተማማኝ ሁኔታ ታልፎ አገራችን በርግጥም የተነደፈላትን የለውጥ ራእይ ተግባራዊ እንድታደርግ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አንድነትና የትግል መንፈስ እንድንረባረብ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለመላ የአገራችን ህዝቦችና ለታላቁ መሪያችን ለአቶ መለስ ዜና ቤተሰቦች መጽናናትን ይመኛል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር