ሲዳሙ ኣፎ ጭምሮ በ25 ቋንቋዎች የትምህርት መዛግብተ ቃላት እየተዘጋጁ ነው


ሐዋሳ (ኢዜአ)፡- የትምህርትን ጥራት በየደረጃው ለማረጋገጥ መንግሥት የሚደርገውን ጥረት ለማገዝ በኢትዮጵያ 25 የብሔረሰብ አፍ መፍቻ ቋንቋዎች የተጀመረው የትምህርት መዝገበ ቃላት ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የመዝገበ ቃላቱ ዓላማና አስፈላጊነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በደቡብ ክልል ደረጃ የትምህርት ባለሙያዎች የተሳተፉበት የሁለት ቀናት አውደ ጥናት በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡
መዝገበ ቃላቱ እየተዘጋጀ ያለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ20 ዓመታት በላይ የማስተማር ልምድና ዕውቀት ባላቸው ምሁራን ከሁለት ዓመት በፊት በተቋቋመው ስፖትላይት የትምህርት ማበልጸጊያ ማዕከል በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ትብብር መሆኑ ተገልጿል። 
የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመዲን በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት የትምህርት ጥራትን በየደረጃው ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የትምህርት መፃሕፍት ግብአት አቅርቦት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
በክልሉ 14 ቋንቋዎች ሳቢና ማራኪ አቀራራብ ለህጻናት አመቺ በሆነ መልኩ ከተዘጋጁት የትምህርት መጻህፍት መካከል በ10 የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የቀረቡት በዝርዝር ታይተው ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡ 
በአሁኑ ወቅት የደቡብ ክልል ቋንቋዎችን ጨምሮ በሀገር ደረጃ በ25 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እየተዘጋጁ ያሉት የትምህርት መዘገበ ቃላት የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ አስተዋጾኦ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ብርሃኑ ቦጋለ እንዳስረዱት በኢትዮጵያ 25 ቋንቋዎች የትምህርት መዝገበ ቃላት መዘጋጀተው ለትምህርት ጥራት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ከተማሩ በኋላ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመማር እንደሚገደዱ ዶክተር ብርሃኑ ገልጸው በዚህም ከፍተኛ የሚባል የአንብቦ መረዳት፣ መጻፍና ማንበብ ችግር እንዳለባቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ባካሄዷቸዉ ጥናቶች ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል።
ችግሩን ለመፍታት በ25 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ለሚማሩ ህፃናት በዓይነታቸው ለየት ያሉ፣ ደረጃቸውን የሚመጥኑና በአብዛኛው በስዕል የተደገፉ መዛግብተ ቃላት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የማዕከሉ አባል የሆኑት ዶክተር ኑር መሐመድ በበኩላቸው የመዛግብተ ቃላቱ አዘገጃጀት በራስ ቋንቋ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ መሆኑን ጠቁመው በኢትዮጵያ በርካታ መዝገበ ቃላት ቢታተሙም ተማሪ ተኮርና የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ዕውቀት ለማጎልበት የሚያግዙ መዝገበ ቃላት በስፋት አልተዘጋጁም፡፡
የአዳዲሶቹ መዝገበ ቃላት ዓላማ በተማሪዎቹ ላይ ያተኮሩ፣ በጥንቃቄ የተመረጡ፣ የተማሪዎችን ደረጃ የሚመጥኑ፣ የሀገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት የተከተሉ የተማሪው ዕውቀትና የትምህርት ደረጃ ያገናዘቡ ናቸው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር በሃዋሳ ከተማ ባዘጋጀው አውደጥናት ላይ ከክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች፣ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከትምህርት ጋር ተያያዥት ያላቸው ባልድርሻ አካላትና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። 
ምንጭ፦http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=headline&newsId=8913

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር