ተቋሙ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ1ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ሊያበድር ነው


አዋሳ ነሐሴ 05/2004 በደቡብ ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት ቁጠባን መሰረት ያደረገ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር ገንዘብ ለተጠቃሚዎች ማመቻቸቱን የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም አሰታወቀ፡፡
በክልሉ በሚገኙ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች የተጀመረው የቁጠባ ኤክስቴንሽ አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል፡፡
የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሀላፊ አቶ ሰሎሞን ገለቱ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ብድሩ የተመቻቸው ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ተደራጅተውና በግል ስራ ፈጥረው ለሚንቀሳቀሱ ከ200 ሺ በላይ ተጠቃሚዎች ነው፡፡
ለስራቸው ማጠናከሪያና ማንቀሳቀሻ የሚሰራጨው ይሄው የብድር ገንዘብ ለእያንዳንዳቸው ከ5 ሺ እስከ 100 ሺ ብር የሚሰጥ መሆኑን አመልከተው ሰርተውበት ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ተመላሽ እንዲያደርጉ የክትትልና የሙያ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተመሳሰይ ሲሰጥ የቆየው የብድር ገንዘብ በአብዛኛው ተመላሽ መደረጉን ያመለከቱት ኃላፊው ህብረተሰቡ የወሰደውን የብድር ገንዘብ በአግባቡ በመጠቀም በወቅቱ የመመለሱ ባህሉ እየዳበረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከ896 ሺ በላይ አዲስና ነባር ደንበኞች ላይ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ ለማሰባሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ባለፈው የበጀት ዓመት በክልሉ በሚገኙ ቀበሌዎች ባለሙያዎች በመመደብ የተጀመረው የገንዘብ ቁጠባ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሰሎሞን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ ከ3 ሺ በላይ የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች መጀመሩን አመልከተው እስካሁንም ከ120 ሺ በላይ የቁጠባ ሳጥኖች ለተጠቃሚው መሰራጨታቸውን አስረድተዋል፡፡
በእያንዳንዱ ቀበሌ የተመደቡት የቁጠባ ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች ህብረተሰቡ በየተሰማራበት የስራ መስክ ከሚያገኘው ገቢ እንዲቆጥብና የቁጠባ ባህልን እንዲያዳብር ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ በመስጠት አገልግሎቱን ለሁሉም ለማዳረስ አየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ህብረተሰቡም ገንዘቡን የሚቆጥበው በንፍሰ ወከፍ የቁጠባ ሳጥንና ሁለት ቁልፍ ተሰጥቶት ከተቆለፈ በኋላ አንድ መፍቻ በቆጣቢውና ሌላ አንድ መፍቻ ደግሞ በኤክስቴንሽን ባለሙያው እጅ እንደሚሆን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡
በየወሩ መጨረሻ ሳጥኑን በጋራ ከፍተው ሂሳቡን በመቁጠር በደረሰኝ ተረካክበው በዕለቱ ባንክ ተጠቀማጭ እንደሚደረግና ወለድ ያለው የቁጠባ ሂሳብ ደብተርም እንደሚኖራቸው አመልከተዋል፡፡
የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ከተመሰረተበት ከ1989 ጀምሮ በስሩ ባሉት ዋናና ንዑስ ቅርረንጫፎች አማካኝነት እስካሁን 471 ሺ ለሚሆኑ ደንበኞች ወደ ሶስት ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ በብድር መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
የብድር ተጠቃሚዎችንና ሌሎችን ጨምሮ ከ799 ሺ በላይ ደንበኞች እስካሁን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በቁጠባ መሰብሰቡም ተመልክቷል፡፡
የተቋሙ ዓላማ በክልሉ ገጠርና ከተማ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን በገንዘብና በሙያ በማገዝ የቁጠባ ባህልን በማዳበር ስራ አጥነትንና ድህነትን ለመቀነስ መንግስት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ መሆኑም ታውቋል፡፡

http://www.ena.gov.et/story.aspx?ID=1608

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር