የቡና ኤክስፖርት እንቅፋት ገጥሞታል


የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ኢንተርፕራይዝ በሚያካሂደው የመልቲ ሞዳል አሠራር ምክንያት በተፈጠረው ችግር፣ ባለፉት ሁለት ሳምንት ቡና ወደ ውጭ መላክ እንዳላስቻለ ምንጮች ገለጹ፡፡ በ2004 ዓ.ም ዓመት በቡና ንግድ ላይ የተፈጠረው ችግር በአዲሱ በጀት ዓመትም ሊደገም ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡ 

የመልቲ ሞዳል አሠራርን ተግባራዊ ያደረገው ኢንተርፕራይዝ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይም መስተጓጎል እየተፈጠረ መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ 

በ2003 ዓ.ም. ወደ ውጭ የተላከው የቡና መጠን 197 ሺሕ ቶን ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. በአገሪቱ ከፍተኛ የቡና ምርት ቢኖርም ከታቀደው 270 ሺሕ ቶን ውስጥ የተላከው 170 ሺሕ ቶን ብቻ ነው፡፡ 

ይህ ሊሆን የቻለው ንግድ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ጊዜያት የቡና ንግድን በሚመላከት ባወጣቸው መመርያዎች ምክንያት ነው ሲሉ፣ የቡና ነጋዴዎች ጣታቸውን በሚኒስቴሩ ላይ ይቀስራሉ፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ የቡና ነጋዴዎች በውጭ ደንበኞቻቸው ዕምነት እየታጠባቸው መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡ 

“ውል በገባነው መሠረት ቡና ማቅረብ ተስኖን ዓመቱን አጠናቀናል፤” ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የቡና ኤክስፖርተር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

የተፈጠሩት ችግሮች የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥራቱና በጣዕሙ ቢታወቅም፣ በዋጋ ከሁሉም አገር ቡናዎች የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል፡፡ 

ችግሮቹን ከፈጠሩት መካከል ቡና በኮንቴይነር ይላክ መባሉና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል የሚወጣው ጨረታ የፈጠረው የአላላክ ዘዴ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የቡና ላኪዎች ማኅበርና ታዋቂ የቡና ላኪዎች ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በተለያዩ ጊዜያቶች ቢነጋገሩም ችግሩ አልተፈታም፡፡ 

በ2005 በጀት ዓመት ይህንን ችግር ለመፍታት ተስፋ የተጣለው በብሔራዊ የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ላይ ሲሆን፣ በኮሚቴው ትልቅ ውሳኔ እንዲተላለፍ ሊያደርጉ የሚችሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታመማቸው ነጋዴዎቹን አሳስቧል ተብሏል፡፡ 

የብሔራዊ የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ንግድ ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ፣ ግብርና ሚኒስቴርና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይጠቀሳሉ፡፡ 

ኮሚቴውን የሚሰበስቡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲሆኑ፣ በተያዘው ወር መጨረሻ ኮሚቴው ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኮሚቴው የሚሰበሰበው የ2004 ዓ.ም. በጀት ዓመት የኤክስፖርት ሥራ አፈጻጸምን በመገምገም ማስተካከያዎችን ለማድረግ ነው፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር