ፍትህ የተሰኘው ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣ ነው፡፡ “ሲዳማ 2፣ ዳግም የሲዳማ እናቶች እንዳያነቡ /Sidaamu Amuwi Lanyikimeesho Wila’anok Gede” (በላቲን ፊደል የተፃፈው ሲዳምኛ ነው) በሚል ርዕስ በሰኔ 15፣ 2004 ዓ.ም ዕትሙ ከላይ የተጠቀሰውን ለውይይት ቀረበ የተባለ ሰነድ መነሻ አድርጎ ያስነበበው ፅሁፍን በተመለከተ የኢህኣዴግ ደጋፊ የሆነው ኣይጋ ፎረም ተብሎ ከሚታወቀው ወይብ ሳይት የሰጠው ምላሽ።




ሰሞነኛው ውዥንብር
ኢብሳ ነመራ
የደቡብ ብሔር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ ከተማ የሆነችው ሀዋሳ፣ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ የውጭና የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ትኩረት ማረፊያ ሆና ሰንብታለች፡፡ የመገናኛ ብዙሃኑ የሃዋሳ ከተማን አስታከው የሲዳማን ብሄር የሚመለከቱ ጉዳዮችንም አንስተዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃኑ መነሻ፣ ግንቦት 2004 ዓ.ም ማገባደጃ ላይ “ሜትሮ ፖሊታን ከተማችንን እንዴት እንምራት” በሚል በክልሉ መንግስት የቀረበ ጥናታዊ ሰነድ ላይ የተደረገ ውይይት መሆኑንም ነግረውናል፡፡
ጉዳዩን አስቀድሞ ያነሳው ፍትህ የተሰኘው ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣ ነው፡፡ “ሲዳማ 2፣ ዳግም የሲዳማ እናቶች እንዳያነቡ /Sidaamu Amuwi Lanyikimeesho Wila’anok Gede” (በላቲን ፊደል የተፃፈው ሲዳምኛ ነው) በሚል ርዕስ በሰኔ 15፣ 2004 ዓ.ም ዕትሙ ከላይ የተጠቀሰውን ለውይይት ቀረበ የተባለ ሰነድ መነሻ አድርጎ አንድ ፅሁፍ አስነብቦናል፡፡
ፍትህ ከዚህ ቀደም የጋዜጣው አቋም መሆኑን እስኪያሳብቅ ድረስ በብሄር ላይ የተመሰረተውን የኢትዮጰያ የፌደራል አወቃቀር ክፋትና ስጋት ሲሰብከን መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ርዕስ በጋዜጣው አምደኛ ሙሉነህ አያሌው በቀረበው ፅሁፍ ግን ለብሔር ተከል የአስተዳደር ስርዓት ሕልውና ያለውን ተቆርቋሪነት ሊያሳይ ሞክሯል፡፡

የጋዜጣው አዘጋጆች የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከሁለት አስርት አመታት በፊት ከቀበርነው የአንድ ብሄር የበላይነት ሲንፀባረቅበት ከነበረው አሃዳዊ የመንግስት ስርዓት ኑፋቄ ደዌ መፈወሳቸው ደግ በሚስልም፤ የአቋም ለውጡ ዱብዳ ስለሆነ “እንኳን ተፈወሳችሁ” ብዬ ከማጨብጨብ ይልቅ፣ መገለባበጡ ውስጥ የተሰነቀረ አንዳች ጤናማ ያልሆነ ነገር እንድጠረጥር አድርጎኛል፡፡ ተፈውሰው ከሆነ ግን “አምላክ እንኳን ማራችሁ፤ ጨርሶ ይማራችሁ” ብዬ ልመርቃቸው እወዳለሁ፡፡

በሙሉነህ አያሌው ፀሃፊነት ፍትህ ያስነበበን ፅሁፍ የሚጀምረው አስር አመት ወደ ኋላ ተጉዞ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጉባኤን ሪፖርት በመጥቀስ ነው፡፡ “በ1994 ዓ.ም በግንቦት ወር ‘መንግስት ሃዋሳ ከዚያ ቀደም እንደነበረው የሲዳማ ዞን ዋና ከተማነቷ ቀርቶ የክልሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ ብቻ እንድትሆን ውሳኔ አስተላልፏል’ የሚል ዜና የሰሙ የሲዳማ ብሄር ተወላጆች፣ ቅሬታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለፅ ወጥተው በመንግስት ታጣቂዎች ተገድለዋል” ይላል፡፡ ይህ እንግዲህ እነደውንጀላ የቀረበ ነው፡፡

እዚህ ላይ በቅድሚያ መነሳት ያለበት ጉዳይ በወቅቱ “ሀዋሳ የሲዳማ ዞን ርዕሰ መዲናነቷ ሊቀር ነው” ብሎ ያለተጨበጠ ሃሰተኛ ወሬ ነዝቶ ህዝቡን ለህገ ወጥ ነውጥ ያነሳሳው ማንነው?” የሚለወ ነው፡፡ ሀዋሳ የዞን ከተማ መሆኗ እንዲቀር የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ እንኳን ቢሆን፣ ሕዝቡ ቅሬታውን የሚያቀርብበት ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ በመኖሩ ይህንን ሕጋዊውና ተገቢው አካሄድ መከተል ሲቻል ሕገወጥ አመፅ ለበስ ሰልፍ መውጣታቸው ተገቢ አልነበረም ፡፡ ይህ ከአስር ዓመት በፊት የተካሄደው አመፅ ቀመስ ሰልፍ ፣ በሃሰተኛ መረጃ ላይ የተመስረተና ዓላማቸውን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ ባልፈቀዱ ወገኖች አሳሳች ቅስቀሰሳ ተቀነቀብሮ የተመራ ሕገወጥ ድርጊት ነበር፡፡

ፍትህ እንደነገረን ሰላምንና ሕግን ለማስከበር በተወሰደ እርምጃ የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ደርሶ እንኳን ቢሆን፣ ቀዳሚው ተጠያቂ ሀሰተኛ መረጃ በመንዛት ሕዝቡ ውስጥ ውዥንብር ፈጥሮ ለህገወጥ አመፅ ያነሳሳው ወገን ነው፡፡ “ዳግም የሲዳማ እናቶች እንዲያነቡ” በሚል ርዕሱ በሲዳምኛ ተተርጉሞ ከተቆርቋሪነት በመነጨ መንፈስ የተፃፈ የሚመስለው የፍትህ ፅሁፍ፣ ውስጡ ሲመረመር ከ10 ዓመት በፊት ተፈጠረ ያለውን አመፅና የንፁሃን ሰቆቃ እንዲደገም መፈለጉን እንረዳለን፡፡ እንዲያውም ፅሁፍ ለአመፅ ተነሱ የሚል የማነሳሳት ይዘት ያለው ነው፡፡ 

የፍትህ ፅሁፍ “ሜትሮፖሊታን ከተማችንን እንዴት እናስተዳድራት” የሚለው ለውይይት የቀረበ ፅሁፍ፣ “ኢህአዴግ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ለውጥ በሁለት መንገድ ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው 20 አመት ሙሉ ስንንገታገትበት የቆየነውን የብሄር ውክልና አመራር በአፍጢሙ ደፍቶ ሌላ አይነት አስተዳደራዊ ስልትን ለመተካት ሃዋሳን እንደናሙና መጠቀም ሲሆን፣ ሌላኛው ዓላማ ምናልባት በአዋሳ ከተማ ላይ ያለውን የሲዳማዎች የበላይነት አንኮታኩቶ በምትኩ ከተማዋ ያላትን እምቅ የገቢ ሀብት ወደ ፌዴራል ስርዓት ውስጥ ለማስገባት የታለመ ይመስላል፡፡ ይህን ለማድረግ ሲዳማዎችን ከጨዋታው ትንሽ ገለል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሲዳማዎችን ከመድረኩ ለማደብዘዝ ደግሞ የአመራሩን ውክልና በአዲስ ንድፈ ሃሳብ ቀይሮ ብሄሩን መበታተን ያስፈልጋል፡፡” ይላል፡፡

አያይዞም “ኢህአዴግ ሁሉም ብሄሮች በተመጣጠነ መልኩ መወከል ይገባቸዋል የሚለውን የብሔር ፖለቲካ አሁን ላይ እርባና እንደሌለውና በሌላ የተሻለ በሚለው መልኩ መተካት እንዳለበት አምኗል፡፡ አምኗል ስል ሌሎችም ክልሎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ለማለት አይደለም ሲዳማን ብቻ ነው የሚመለከተው” ብሎናል፡፡

በዚህ በሙሉነህ አያሌው በቀረበ ፅሁፍ ላይ የሰፈረ ሃሳብ ውስጥ ሁለት ነገሮችን እናገኛለን፡፡ አንደኛው ፀሃፊው የብሄር ብሄረሰብን መብት ለማረጋገጥ በሕገመንግስቱ ላይ የሰፈረውን ድንጋጌ የማያምኑበትና የሚጠየፉት መሆኑን ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ህዝብን በመንግስት ላይ ለአመፅ ማስነሳት የሚያስችል እስከሆነ ድረስ “የሲዳማን ብሄር ሕዝብ ህገመንግስታዊ ብሄራዊ መብቴ ተጥሶብኛል” የሚል ስጋት አድሮበት በመንግስት ላይ እንዲነሳ የማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑን ነው፡፡

በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ እንዳነሳሁት ፀሃፊ ሙሉነህ አያሌውም ፍትህ ጋዜጣ እንደ አቋም የያዘው መሆኑን እስኪያሳብቅ፣ ሕገመንግስታዊው ብሄር ተከል የመንግስት አወቃቀር ላይ ያለውን ጥላቻ አንፀባርቀዋል፡፡ “. . 20 አመት ሙሉ ስንገታገትበት የቆየነውን የብሄር ውክልና. . . “ በሚል የተገለፀው ይህን በትክክል ያሳያል፡፡ እኛ በሕገመንግስቱ ብሄራዊ መብታችን የተከበረልን ዜጎች፣ በብሄር ውክልናው ስንመራ እንጂ ስንንገታገት አልቆየንም፡፡ ሙሉነህ አያሌው ግን የብሄሮች መብት በመከበሩ ሲንገበገቡ ስለኖሩና ካሁን አሁን ይፈረካከሳል ብልው በጉጉት ሲጠብቁ ስለቆዩ መንገታገት ሆኖ ነው የታያቸው፡፡

ይህን 20 ዓመት “የተንገታገትንበት” ያሉትንና ፀሃፊው ሳያሳቡት እንደማይደግፉት የገለፁትን የብሄር ውክልና፣ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ማድረግ ያስችላል ብለው ሲገምቱ መልሰው “ኢህአዴግ ሊንደው ነው” ብለውናል፡፡ይህንንም “የብሄር ውክልና አመራር በአፍጢሙ ደፍቶ ሌላ አይነት አስተዳደራዊ ስልትን ለመተካት ሃዋሳን እንደናሙና ተጠቅሟል፡፡ በሃዋሳ ላይ ያለውን የሲዳማዎች የበላይነት አንኮታክቶ የከተማውን እምቅ የገቢ ሃብት ወደፌዴራል ስርዓት ለማስገባት ያለመ ነው፣ ኢህአዴግ ሁሉም ብሄሮች በተመጣጠነ መልኩ መወከል ይገባቸዋል የሚለውን የብሄር ፖለቲካ በተለይ በሲዳማዎች ላይ እርባና እንደሌለው ተረድቶ በሌላ ስርአት ሊተካው አልሟል” በማለት ገልፀውታል፡፡

ፀሃፊ ሙሉነህ በመርህ ደረጃ ብሄር ላይ የተመሰረተን የመንግስት አወቃቀርና የሕዝብ ውክልና ስለማይቀበሉ ይህን ያሉት ካላይ እንደጠቀስኩት ለሲዳማ ህዝብ ብሄራዊ መብት ከመቆርቆር ሳይሆን፣ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ አላማ ብቻ ነው፡፡ የክልሉ ምንግስትና የፌደራል መንግስት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ከሰጡት መግለጫ ያገኘነው መረጃ፣ የፍትህ አምደኛ ሙሉነህ አያሌው የነገሩን “ሀዋሳ የሲዳማ ዞን ዋና ከተማ መሆኗ እንዲያከትም ተወሰኗል” በሚል ያቀረቡት ወሬ ነጭ ውሸት ነው፡፡ የፍትህ ፀሃፊ ሙሉነህ አያሌው ስለሲዳማ ብሄር ክልል የመሆን ጥያቄ ብዙም ያሉት ነገር የለም፡፡ በጣም የሚጠሉትና የሚፈሩት ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አመፅ ሊቀየር ይችላል ብሎ የገመተውን ማንኛውንም ጉዳይ በማራገብ አባዜ የተለከፈው የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም በሃዋሳ ከተማ ዙሪያ የተደረገውን ውይይት መነሻ አድርጎ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ አመራሮችን ጠቅሶ ሊያሟሙቀው ሞክሯል፡፡

የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም ሰሞኑን በሃዋሳና በሲዳማ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ፣ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የተባለ ተቃዋሚ “ሜትሮፖሊታን ሃዋሳን እንዴት እንምራ” በሚል ውይይት ተደረገበት የተባለ ሰነድ መነሻ በማድረግ “ በ1984 አምስት የነበሩትን ክልሎች ወደ አንድ በማምጣት አሁን ደቡብ የሚለውን ክልል የፈጠረበት ሁኔታ ድንገተኛ ነበር” ብሎ “የሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል” የሚል አቋም መያዙንም ነግሮናል፡፡ 

ሲዳማ ክልል የመሆን መብቷ ቢከበር “ኢህአዴግ አገሪቱን በጣጠሰ” ብሎ አልቅሶ ለማስለቀስ በቀዳሚነት የሚቆሙት የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ የአማርኛ ፕሮግራም ጋዜጠኞችና የፍትህ ጋዜጣ ባለቤቶችና አዘጋጆች፣ ባልተጨበጠ መረጃ የሲዳማን ህዝብ “ብሄራዊ መብትህ ተጥሷል” ብለው በመንግስት ላይ ለማነሳሳት ያስችላል በሚል ግምት የገለፁትን አቋም ከኢፌዴሪ ሕገመንግስት አኳያ እንመልከተው፡፡

የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም የሲዳማ አርነት ግንባር የተሰኘውን ፓርቲ ጠቅሶ፣ “ኢህአዴግ አምስቱን የደቡብ ክልሎች የሚመለከታቸውን ሳያማክር በ1984 ድንገት ደቡብ ወደተሰኘው ክልል ቀይሯል” ከሚለው ልጀምር፡፡

በ1984 ዓ/ም የነበረው የሽግግር መንግስት መዋቅር በወቅቱ እንደ ሕገ ምንግስት በሚያገለግለው ቻርተር የተወሰነ ነበረ፡፡ በወቅቱ የሲዳማ አርነት ንቅናቄና ሌሎች የሲዳማ ብሄር ተወካይ ድርጅቶች እንዲሁም የተቀሩት የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ተወካዮች የሽግግር መንግስቱ ም/ቤት ውስጥ አባላት ነበሩ፡፡

የዚህ አይነት ውሳኔ ከዚህ ም/ቤት ውሳኔ ውጭ ኢህአዴግ እንደ አንድ የም/ቤቱ አባል እንደሆነ ፓርቲ ለብቻው ሊወሰንበት የሚያስችለው ስልጣን አልነበረውም፡፡ እኔ እንደ አንድ ዜጋ እስከማውቀው ድረስ በኢፌዴሪ ሕገመንግስት እስኪወሰን ድረስ አምስቱ የደቡብ ኢትዮጰያ ክልሎችን ጨምሮ አስአራቱም የሽግግር መንግስቱ የአስተዳደር መዋቅሮች በስራ ላይ ነበር የቆዩት፡፡

የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት እንደ አንድ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል የተዋቀረው በኢፌዴሪ ህገመንግስት እንጂ በሽግግር መንግስቱ ቻርተር ወይም በኢህአዴግ ውሳኔ አይደለም፡፡ እነዚህ እውነታዎች አሁን በመንግስት/ ኢህአዴግ ላይ የቀረበውን ውንጀላ መሰረተ ቢስ ያደርጉታል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገመንገስት ከመፅደቁ በፊት የሲዳማን ሕዝብ ጨምሮ ሁሉም የደቡብ ኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በተደጋጋሚ መክረውበታል፡፡ ሕገመንግስቱን ባፀደቀው ምክር ቤት ውስጥም በቀጥታ የመረጡዋቸው ተወካዮቻቸው ተሳትፈዋል፡፡ እናም የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የፌደራል ምንግስቱ ኣባል ከሆኑት ዘጠኝ ክልሎች አንዱ የሆነው በዘፈቀደ ውሳኔ ሳይሆን በሲዳማ ሕዝብ ፍቃድና ውሳኔም ነበር፡፡
5
አሁን የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የተሰኘው ድርጅት “የሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ሊከበር ይገባል” ማለቱንም ቪኦኤ ነግሮናል፡፡ የሲዳማ ብሄር እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ፣ ሕዝብ በማንኛውም ግዜ የራሱን ክልል የማቋቋም መብቱ በኢፌዴሪ ሕገመንግስት ተረጋግጧል፡፡ ሕገመንግስቱ በአንቀፅ 47 ንኡስ አንቀፅ 2 ላይ “በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ 1 የተመለከቱት ክልሎች (የዘጠኙን የኢፌዲሪ አባል ክልሎችን ማለት ነው) ውስጥ የተከተቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛው ግዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው” ይላል፡፡ በመሆኑም የሲዳማ ብሄር በዚህ የህገመንግስት ድንጋጌ መሰረት በክልል የመዋቀር መብት አለው፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ በክልል የመዋቀሩ ጥያቄ በማን ነው የሚቀርበው? አፈፃፀሙስ እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡

ክልል የመሆኑን ጥያቄ ማንሳት የሚችለው እንደ ሲዳማ አርነት ንቅናቄ ያለ አንድ ፓርቲ ወይም ቡድን ሳይሆን፣ የብሄሩ/የብሄረሰቡ ህዝብ ነው፡፡ አፈፃፀሙም ጥያቄው ከሕዝቡ የተነሳና የሕዝቡ ብቻ መሆኑን በሚያረጋግጥ አኳኋን የሚከናወን ነው፡፡

የ ኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 3 ይህን የሚመለከት ድንጋጌ ይዟል፡፡
በዚህ አንቀፅ መሰረት፣ “የማንኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመስረት መብት ስራ ላይ የሚውለው፤
ሀ. ክልል የመመስረት ጥያቄው በብሄሩ፣ በብሄረሰቡ ወይም በሕዝቡ
ም/ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና
ጥያቄው በፅሁፍ ለክልሉ ም/ቤት ሲቀርብ፣
ለ. ጥያቄውን የቀረበለት የክልል ም/ቤት ጥያቄው በደረሰው አንድ አመት ግዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ህዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣
ሐ. ክልል የመመስረት ጥያቄው በብሔር፣ በብሄረሰቡ ወይም ሕዝቡ እዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፣
መ. የክልሉ ም/ቤት ስልጣኑን ለጠየቀው ብሄር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብ፣
ሠ. በሕዝብ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው፡፡
እናም ስለ ሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ሲነሳ ጉዳዩ በቅድሚያ መታየት ያለበት የብሄሩ ህዝብ ጥያቄውን አንስቷል ወይ? ከሚለው አኳያ ነው፡፡ የሲዳማ ብሄር ተወካይ የሆነው የዞኑ ም/ቤትና ዞኑ አባል የሆነበት የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት እስካሁን ይህ ጥያቄ እንዳልቀረበላቸው በይፋ አስታውቀዋል፡፡

አሁን ደግሞ ሲዳማና ሃዋሳ የሰሞኑ የቪኦኤና የፍትህ ትኩረት እንዲሆኑ ወዳደረገው “የሃዋሳ ከተማ በፌደራል መንግስት ስር ልትሆን ነው” ወደሚል ጉዳይ እንመለስ፡፡ ሁለቱ ሚዲያዎች በሃዋሳ ከተማ ዙሪያ የሰጡት አስተያየትና ያቀረቡት ዘገባ መንግስት የሃዋሳን ከተማ ከሲዳማዎች ላይ ሊነጥቅ ነው የሚል ሃሳብ ያዘለ ነው፡፡

ፍትህና የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ፕሮግራም በሃዋሳ ከተማ ዙሪያ፣ ሀዋሳን እንደ ሜትሮፖሊታን ከተማ ከማስተዳድር ውክልና ጋር በተገናኘ የተነሳውን ጉዳይ ለውይይት ከቀረበው ሰነድ ይዘት ጋር አያይዤ ለማንሳት በቀጠሮ ትቼ፣ “ሀዋሳ በፌደራል መንግስት ስር ልትሆን ነው” በሚል የተናፈሰውን ወሬ በእጭሩ እንመልከተ፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በቅድሚያ መታየት ያለበት፣ የፌደራል መንግስት በክልሉ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ ከተሞችን የፌደራል መንግስቱ አካል የማድረግ ሕገ መንግስታዊ ስልጣን የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ሀዋሳ ከተማን የመውሰድ የውሳኔ ሃሳብ ባልቀረበበት ሁኔታ አሉባልታ ላይ ተመስርቶ እየተሰነዘረ ያለው አስተያየት ተገቢነት የለውም፡፡

የፌደራል መንግስት እንኳን በክልል መንግስታት ስር ያሉ ከተሞችን በራሱ ስር እንዲሆኑ መወሰን ቀርቶ፣ በአንድ ክልላዊ ምንግስት ውስጥ ሲተዳደር የቆየ በሄር፣ ብሄረሰብ፣ ሕዝብ ከክልሉ ተነጥሎ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ክልል የመመስረት ጉዳይ ውስጥ እንኳን ጣልቃ የመግባት ሕገመንግስታዊ ስልጣን የለውም፡፡ እዚህ ላይ የሚኖረው ድርሻ ከላይ በተጠቀሰው የሕገ መንግስት አነቀፅ መሰረት ብሄሩ/ ብሄረሰቡ ክልል ሆኖ ራሱን ችሎ ሲዋቀር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እውቅና መስጠት ብቻ ነው፤ በቃ፡፡

እናም ሀዋሳ ከክልሉም፣ ከሲዳማ ዞንም ተነጥቃ በፌደራል ምንግስት ስር ልትሆን ነው የሚለው ወሬ አግባብነተ ያላቸውን ሕጎች ያላገናዘበና መሰረተ ቢስ ነው፡፡ ዓላማውም ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ ከትቶ ተገቢ ባልሆነ አኳኋን መንግስትን እንዲቃወም ማነሳሳት ነው፡፡ የሲዳማ ብሔር ሕዝብ፣ ሌሎች የደቡብ ክልልና የተቀሩት የኢትዮጵያ ክልሎች ሕዝቦች በዚህ ሰሞነኛ የነውጠኞች ውዥንብር ላለመጠለፍ ማስተዋል ይገባዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር