በሲዳማ ዞን ጭኮ ወረዳ የተነሳው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው



ሰኔ ፲፱ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት የወረዳው የመረጃ ምንጭ እንደገለጠው ተቃውሞው የተነሳው ዛሬ 4 ሰአት ላይ ነው። በትናንትናው እለት እንደዘገብነው የካናዳ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በቅርቡ በሲዳማ ዞን የተነሳውን ተቃውሞ ያነሳሱት ባለሀብቶችና ተቃዋሚዎች ናቸው በማለት የተናገሩትን ለመቃወም ነበር ዛሬ ሰለማዊ ሰልፉ የተጠራው።
አቶ ሽፈራው ያደረጉትን ንግግር ያስቆጣቸው የጭኮ ወረዳ ነዋሪዎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሰለማዋዊ ሰልፍ ለማድረግ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄያቸውን ወረዳው አስተዳዳሪ ለሆኑት ለአቶ አሻግሬ ጀምበሬ ደብዳቤ አስገብተው ነበር። በዚህም መሰረት ዛሬ ጧት የተቃውሞ ሰልፉን ለማካሄድ ወደ ስታዲየሙ ሲያቀኑ የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ ክፍሌ የፌደራል ፖሊስ በመጥራት የህዝቡ መሪዎች እንዲያዙ አድርገዋል።
የከተማው ነዋሪ ተወካዮችን ለማስለቀቅ ከፌደራል ፖሊስ አባላት ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ ፖሊሶች ለተቃውሞ የመጣውን ሰላማዊ ሰው በቆመጥ እየደበደቡ ለመበትን ሲሞክሩ ቆይተዋል። ከሰአት በሁዋላ የከተማው ህዝብ በነቂስ በመውጣት የታሰሩት መሪዎች እንዲፈቱለት ፖሊስ ጣቢያውን በመክበብ ጥያቄውን አቅርቧል። ስቱዲዮ እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ህዝቡ የፖሊስ ጣቢያውን እንደከበበ ነበር።
ህዝቡን ውስጥ ለውስጥ ለአመጽ እንዲነሳ አድርገዋል በሚል የወረዳው ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ዘላለም ላላም ታስረዋል። እንዲሁም ከመንግስት ሰራተኞች መካከል አቶ ገረመው ፊሳ፣ አቶ ኤፍሬም ተፈራ፣ ኢዛ እንዳለና ንጉሴ ታደሰ የታሰሩ ሲሆን፣ ባለሀብቱ አቶ አስቻለው በቀለም ታስረዋል።
አቶ ገረመው ፊሳ፣ አቶ ኤፍሬም ተፈራ፣ አቶ ኢዛ እንዳለና አቶ ንጉሴ ታደሰ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ስለተፈጸመባቸው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ተኝተዋል።
ከሳምንት በፊት በዚሁ ወረዳ በተነሳው ተቃውሞ 2 ሰዎች መገደላቸውን፣ 2ቱ ደግሞ ክፉኛ ቆስለው የደረሱበት አለመታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።
በሲዳማ ዞን የተነሳው ተቃውሞ በቀላሉ ሊበርድ እንደማይችል ብዙዎች ይናገራሉ። የሲዳማ ተወላጆች እንደሚሉት ጥያቄያቸው ፍትሀዊና የመብት ጥያቄ ቢሆንም፣ የመንግስት ባለስልጣናት ጉዳዩን ወደ ዘር ፖለቲካ በመውሰድ ህዝቡ እርስ በርሱ እንዲተላለቅ ለማድረግ ይሞክራሉ በማለት ይናገራሉ።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር