በሀዋሳ የጎብኚዎች ቁጥርና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ እየጨመረ ነው



ሃዋሳ, ሚያዝያ 16 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - ዜና ትንታኔ
በደቡብ ኢትዮጵያ ሰምጥ ሸለቆ የምትገኘው ሀዋሳ ለቱሪስቶች ምቹና ተመራጭ ከተማ እየሆነች መምጣቷን የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎቿና አስተናጋጆቿ ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ ሀዋሳ ከተማ ጎራ ብለው የቆዩት ቻይናዊው ሚስተር ጆ ጂን እና ኬንያዊው ሚስተር ኒልሰን ቴምሊ የሀዋሳ ሃይቅ፣የአካባቢው የተፈጥሮና መልከአድራዊ አቀማመጥ፣ሀይቁ ዳር የሚገኘው የሌዊ ሪዞርትና መዝናኛ ፣የህዝቡ እንግዳ አቀባበል ስርአት እንደተመቻቸውና እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
የከተማው ንጽህናና ውበት፣በመገንባት ላይ ያሉ አዳዲስ ህንፃዎች ፣ምቹ የመናፈሻ ቦታዎችን ጨምሮ ሀዋሳ ለኑሮ ተስማሚ በመሆኗ ወደፊትም የመዝናኛ ምርጫቸው እንደሆነች ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ለመዝናናት ወደ አዋሳ ያቀኑት አቶ ኩቲ ኢታይ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ማረፊያቸውን ሌዊ ሪዞርት በማድረግ የሀዋሳ ሃይቅ ላይ በዘመናዊ ፈጣን የጀልባ ሽርሽር አሳን በማስገር እንዲሁም የሆቴሉ መስተንግዶና አገልገሎት ምቹ በመሆኑ ትዳር ሲይዙ እዚሁ ለማሳለፍ ምርጫቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በከተማውና አካባቢው ያሉት ተፈጥሮአዊ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ለመጎብኘት የሚመጣው የቱሪስት ፍሰትና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚገልጹት የከተማው ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የመረጃና ፕሮሞሽን ባለሙያ ወይዘሮ እታፈራሁ ተምትም ናቸው፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 97 ሺህ 187 የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ተስተናግደው ከ22 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ፡፡ ከጎብኚዎቹም መካከል ከ21 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በጎብኚዎች ብዛት ከሁለት እጥፍ በላይ እና በገቢም ረገድ ከአምስት እጥፍ በላይ እንደሚበልጥ አስታውቀዋል፡፡
የሀዋሳ ሃይቅና በቅርቡ የተገኘው የሀዋሳ ሃይቅ ደሴት ፣በውስጡና አካባቢው ያሉ ብርቅዬ አእዋፍ ፣የጉማሬ መንጋ ፣ጥንታዊ ቤተመንግስት፣ የአሳ ገበያ፣ትክል ድንጋዮች፣ የአትሌት ሀይሌና የሌዊ ሪዞርትን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ የሆቴልና ቱሪዝም አገልገሎት መስጫ ተቋማትን በመገናኛ ዘዴዎች በማስተዋወቅ ለቱሪስቶች ፍሰትና ለገቢው መጨመር የተከናወኑ ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በተለይ ሆቴልና ቱሪዝም መስተንግዶን በተመለከተ ለ62 ተቋማት የአገልገሎት ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ከመሰጠቱም ሌላ ለአምስት የአካባቢው አስጎብኚዎች ስልጠና በመስጠት እንዲሰማሩ መደረጉም ታውቋል፡፡
ሀዋሳ የኮንፍራንስ ቱሪዝም ከተማ እንድትሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ መመረጧ ሀገራዊ፣አሁጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባዔ የማዘጋጀት አቅም በመገንባት የቱሪስቶች ፍሰትና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እንዳስቻለ ተገልጿል፡፡
የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተለይ የምሽት መዝናኛ ክበባት ከመኖሪያ አካባቢ፣ ከትምህርትና ጤና ተቋማት ጋር በተያያዘ ሊኖራቸው የሚገባው አያያዝ ደንብና መመሪያ የተከተለ እንዲሆን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ስርዓት የሚይዙበት ሁኔታ መመቻቸቱን ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡
የሌዊ ሪዞርት ማርኬቲንግ ማኔጅመንት ክፍል ሃላፊ አቶ አሮን ካሳዬ በበኩላቸው ድርጅታቸው በከተማው ሁሉም እንደአቅሙ የሚስተናገድባቸው ደረጃቸውን የጠበቁ አራት ሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት መስጫ አለው ብለዋል።
በተለይ በሀዋሳ ሃይቅ ዳር ያስገነቡት ዘመናዊ ሪዞርት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መገልገያ አመቻችቶ እያስተናገዱ ካሉት የውጭ ቱሪስቶች መካከል የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የኤሽያእና አፍሪካ ሀገራት ዜጎች እንደሚገኙበት አስታውቀዋል፡፡
ሀዋሳ ለቱሪስት ምቹና ተመራጭ መሆኗን ቱሪስቶቹ በሚሰጧቸው አስተያየት መራdታቸውን ገልጸው እስካአሁንም ለቱሪስቶች በሚሰጡት አገልገሎት እስከ 200 ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/AmharicNews/2012/Apr/24Apr12/164293.htm

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር