የዓለም ቡና ዋጋ ማሽቆልቆል በአገር ውስጥ ግብይት ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው



በዓለም የቡና ዋጋ ማሽቆልቆል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፈው ሳምንት እስከ 12 በመቶ ድረስ አውርዶት የነበረውን ዝቅተኛውን የመገበያያ ዋጋ ገደብ እንደገና ወደ አምስት በመቶ እንዲወርድ አደረገ፡፡
ምርት ገበያው ባሳለፍነው ሳምንት ዝቅተኛውን የግብይት ወለል ወደ 12 በመቶ እንዲወርድ ያደረገው፣ በዓለም አቀፍ ገበያ የቡና ዋጋ እየወረደ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የአገር ውስጥ ግብይትም በተመሳሳይ ሁኔታ መቀነስ ይጠበቅበት ስለነበረ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው ዓለም አቀፍ የቡና የዋጋ ማሽቆልቆል በአገር ውስጥ ያለውን የግብይት ዋጋ ከዓለም አቀፉ ገበያ በላይ እንዲሆን አስገድዶት ነበር፡፡

ይህም በመደረጉ በሁለት ቀናት ውስጥ የቡና ዋጋ እንዲወርድና የመጫረቻ ዋጋውም በኒውዮርክ ገበያ ካለው ዋጋ ጋር ተቀራራቢ እየሆነ በመምጣቱ፣ ለሁለት ቀናት የተሠራበት የመገበያያ ገደብ ተመልሶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን ዶ/ር እሌኒ አስረድተዋል፡፡

በምሳሌ ያቀረቡትም ባለፈው ሳምንት አንድ ሺሕ ብር ዋጋ የነበረው ቡና ከለውጡ በኋላ ዋጋው ወደ 900 ብር እንዲወርድ ሆኗል በማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ግብይቱ 900 ብር ዋጋን ይዞ ከአምስት በመቶ ወደላይ ወይም ወደታች ሳይወርድ የቡና ጨረታው የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ይህም አሁን እየወረደ ካለው ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ጋር እንዲጣጣም ያደርገዋል ተብሏል፡፡

የአገር ውስጥ ግብይትን ከኒውዮርክ ገበያ ዋጋ ጋር ለማጣጣም ሲባል ባለፈው ሳምንት የተወሰደው ዕርምጃ፣ የአገር ውስጥ ዋጋን እንዲወርድ በማድረጉ እንደገና የዋጋ ገደቡን ወደ አምስት በመቶ እንዲወርድና ግብይቱ በዚሁ መንገድ እንዲቀጥል የተደረገ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንዲህ ዓይነት አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራበት መሆኑን የሚጠቁሙት ዶ/ር እሌኒ፣ በአገር ውስጥ የሚደረገው የቡና ግብይት ከኒውዮርኩ ዋጋ እየበለጠ መሄዱ ወደ ግብይት ማዕከሉ በሚቀርበው የቡና መጠን ላይ ተፅዕኖ እያሳረፈ መጥቶ እንደነበር ታውቋል ብለዋል፡፡

በአገር ውስጥ ያለው ግብይትና በኒውዮርኩ ዋጋ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት አቅራቢዎች ቡናን ወደ መያዝ ጭምር እያደረሳቸው በመሆኑ፣ ሊከተል የሚችለውን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ምርት ገበያው የቡና ዋጋን ከኒውዮርኩ ዋጋ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ ወሰድኩ ያለውን ዕርምጃ ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት፣ በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፉ የቡና ዋጋ እየወረደ በመሆኑ፣ በዚሁ መሠረት አቅራቢዎች ዋጋቸውን እንዲያስተካክሉ ተሰጥቶ የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ብዙም ውጤት ሊያመጣ ስላልቻለ የግብይት ዋጋ ወለሉን እስከ 12 በመቶ በማውረድ ዋጋው እንዲወርድ ተደርጓል ይላሉ፡፡ በዚህ መሠረት በዚህ ሳምንት በተደረገ ግብይት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና እንዲቀርብ ማስቻሉንም የዶ/ር እሌኒ ገለጻ ያስረዳል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት የኒውዮርክ ዋጋ ወደ ዘጠኝ በመቶ ሲወርድ የአገር ውስጥ ግን የቀነሰው 1.5 በመቶ ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር እሌኒ፣ ይህ ሰፊ ልዩነት በመሆኑ ይህንን በማጥበብ የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል፡፡

አሁን ያለው የግብይት ዋጋ ከኒውዮርክ ዋጋ ጋር የተመጣጠነ ሆኖ በመገኘቱ የግብይት ገደቡ ወደ አምስት በመቶ እንዲመለስ ቢደረግም፣ በርካታ ላኪዎች የመጫረቻ ዋጋው ከዚህም በታች ሊቀንስ ይገባል እያሉ መሆኑም ታውቋል፡፡

አቅራቢዎች ደግሞ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ እኛን ይጐዳናል እያሉ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር እሌኒ፣ ዓለም አቀፉ የቡና ዋጋ አሁን ካለበት በታች እየወረደ ከመጣ እንደገና ተመሳሳይ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

አቅራቢዎችም ይህንን በመረዳት የያዙትን ቡና ለገበያ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ተገልጾ፣ በዚህ ሳምንት ወደ ግብይት ማዕከሉ ለጨረታ የቀረበው ቡና መጠን ከፍ ሊል ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመገበያያ ገደቡ ላይ ለውጥ ሲደረግ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን፣ በተለይ የብር የምንዛሪ ለውጥ በሚደረግበት ወቅት የመገበያያ ገደቡን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር እንዲጣጣም የሚያደርግ ዕርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡

መንግሥት በያዝነው ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ያቀደ ቢሆንም፣ የግማሽ ዓመት የንግድ አፈጻጸሙ ከዕቅድ በታች እጅግ የወረደ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በግማሽ ዓመቱ በጥቅል ከቡና የወጪ ንግድ 300 ሚሊዮን ዶላር ያገኘ ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት ከተመዘገበው የሙሉ ዓመት አፈጻጸም 841 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ዕቅዱን ለማሳካት የሚያስቸግር መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡  

በተለይ ከወራት ወዲህ እየወረደ ያለው የቡና ዋጋ የዕቅዱን ስኬት በመፈታተን ትልቁን ድርሻ ይዟል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር