በሀዋሳ ከተማ የተገነቡ አንድ ሺህ 675 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች በእጣ ተላለፉ



አዋሳ, ጥር 5 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በሀዋሳ ከተማ በ200 ሚልዮን ብር የተገነቡ አንድ ሺህ 675 የጋራ መኖሪያና ንግድ ቤቶች ዛሬ ተመዝግበው ለሚጠባበቁና ቅድመ ክፍያ ላጠናቀቁ ግለሰቦች በእጣ ተላለፈ፡፡
መንግስት ባመቻቸው የቤቶች ልማት የመኖሪያ ቤት ባለቤት በመሆናቸው መደሰታቸውንም ተጠቃሚዎች ገልጸዋል፡፡
በሀዋሳ ከተማ አራት አካባቢ ተገንብተው በእጣ ለነዋሪዎች ከተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል አንድ 575 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቀሪዎቹ 100 የንግድ ቤቶች መሆናቸውን የከተማው ከንቲባ አቶ ዮናስ የሱፍ በዕጣው ስነ ስርዓት ላይ አስታውቀዋል፡፡
ሶስት ደረጃ ያላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች መንግስት የተጠቃሚዎችን የመክፈል አቅም በማየት ያደረገውን ከፍተኛ ድጎማና ድጋፍ ሳይጨምር ከንግድ ቤቶቹ ጋር 200 ሚልዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የተቀናጀ የቤቶች ፕሮግራም በከተሞች ልማት ስራ ውስጥ ለቤቶች ልማት ልዩ ትኩረት የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም የሚመጥን የቤት ልማት ስራ በማከናወን የመጠለያ ችግርን መቅረፍ፣ የቁጠባ ባህልን በማዳበር ሰፊ የስራ ዕድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር በኩል ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
በከተማው ቀደም ሲልም የአንድ ሺህ 648 የጋራ መኖሪያና ንግድ ቤቶች ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን ገልጸው ግንባታቸው 95 በመቶ የተጠናቀቀና ዕጣ የወጣላቸው 1 ሺህ 575 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መጋቢት 15/ 2004 ለባለዕድሎች እንደሚተላለፉ አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ስራ አጥነትን የመቅረፍ አላማ እንዳለው ገልጸው በእስካሁኑ ሂደት ለ5ሺህ 985 ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡
የደቡብ ክልል ቤቶች ልማት ኤጄንሲ ዋና ስራ አስኪያ አቶ ወንድሙ ሴታ ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ዘጠኝ ከተሞች በከፍተኛ የመንግስት ድጎማና ወጪ የተጠናቀቁ 4 ሺህ 884 ቤቶች ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን ጠቁመው በግንባታ ላይ የሚገኙ 3 ሺህ 280 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እስከ መጋቢት 2004 በማጠናቀቅ ለተጠቃሚው ለማስተላለፍ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ባህል አዳራሽ ዛሬ ዕጣ ከደረሳቸው ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ በግለሰብ ቤት ይደርስባቸው የነበረው ስቃይና ችግር በቤቶች ልማት ተቃሎ የቤት ባለቤት ለመሆን በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
እጣ ያልደረሳቸው ግለሰቦች የዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓቱ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ግልፅና ፍትሃዊ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም የቤቶች ልማት አሁን የጀመረውን ስራ አስፋፍቶና አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር