ኬንያዊው በሐዋሳ ክብረወሰን አስመዘገበ

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ‹‹ሁሉም›› በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ሁለተኛው የሐዋሳ ኢንተርናሽናል ግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኬንያዊው አትሌት ኪፕሊሞ ኪሙታይ በአገሩ ልጅ የተያዘውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸንፏል፡፡ በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ የኦሜድላ አትሌት ሲሳይ መአሶ አሸናፊ ሆናለች፡፡

የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ‹‹ሁሉም›› በሚል ቃል የተዘጋጀው የእናቶችንና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስና ለማስቀረት የሚያስችሉ መልዕክቶች እንዲተላለፉበት በሚል ሲሆን፣ በውድድሩ ከአትሌቶች ውጪ ከአራት ሺሕ በላይ በሩጫው ተሳትፈዋል፡፡ ውድድሩን የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ፣ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴና ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም አስጀምረውታል፡፡

በአትሌቶች መካከል በተደረገው 21 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ኬንያዊው ኪፕሊሞ ኪሙታይ ርቀቱን 1 ሰዓት 03 ደቂቃ 10 ሰኮንድ በሆነ ጊዜ ሲያጠናቅቅም፣ ይህም ባለፈው ዓመት በሌላው ኬንያዊ ዊልስ ቼሮት 1 ሰዓት 03 ደቂቃ 13 ሰኮንድ ተይዞ የቆየውን በ03 ሰኮንድ በማሻሻል አዲስ ክብረወሰን አሻሽሏል፡፡

በሴቶች መካከል በተደረገው የኦሜድላዋ አትሌት ሲሳይ መአሶ በ1 ሰዓት ከ16 ደቂቃ 41 ሰኮንድ አጠናቃ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለሁለቱም አትሌቶች የ10 ሺሕ ብር ሽልማት ሲሰጥ፣ ኬንያዊው ኪፕሊሞ ከሙታይ ለክብረወሰኑ ተጨማሪ የ3 ሺሕ ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር