በዲላ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ረብሻ አስነስተዋል›› በሚል የተጠረጠሩ ተማሪዎች ክስ ተመሠረተባቸው

ለ‹‹ስድስት ቀናት ፖሊስ ጣቢያ ስንታሰር ፍርድ ቤት አልቀረብንም››  ተማሪዎች
‹‹በሕጉ መሠረት ፍርድ ቤት አቅርበናቸዋል››  የዲላ ከተማ ፖሊስ


(በታምሩ ጽጌ) ከአዲስ አበባ 338 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኅዳር 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ተነስቶ ለነበረውና በልዩ የፖሊስ ኃይል በቁጥጥር ሥር ለዋለው የተማሪዎች ረብሻ ላይ በመሳተፍ፣ በማነሳሳትና ጉዳት በማድረስ በተጠረጠሩ ሁለት ተማሪዎችና ሌሎች ሦስት ግለሰቦች ላይ በትናንትናው ዕለት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

በከሳሽ መርማሪ ፖሊስ በዲላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ የተመሠረተባቸው የሦስተኛ ዓመት የቋንቋ ተማሪ በሆኑት ተማሪ ሜላት ዓይናለም፣ ተማሪ ምዕራብ አለማየሁ፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ባልሆኑት ሚሊዮን ምንጊዜም ግዛቸው፣ ፍጹም ብዙአየሁና አብዱ አቡበከር ላይ መሆኑን የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡

በዲላ ከተማ መግቢያ ዳርቻ ላይ የተመሠረተው የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ካምፓሶች ሲኖሩት፣ ረብሻው የተነሳው ኦዳአያ (አዲሱ ካምፓስ) በሚባለው ውስጥ ሲሆን፣ የረብሻውም መነሻ በአንድ ተማሪ ላይ በደረሰ ድብደባ ምክንያት መሆኑን ክሱ ያመለክታል፡፡

ኅዳር 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ከጠዋቱ 5፡30 ሰዓት ሲሆን ተማሪዎች ፈተና ጨርሰው ይወጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ቀድሞ የወጣ ተማሪ (ምንተስኖት ጌቱ) ጋር በተፈጠረ ግጭት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በተንቀሳቃሽ ስልክ ከትምህርት ቤቱ ውጭ ያሉትን 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በመጥራት ተማሪውን በማስደብደባቸው ሆን ብለው አስበው፣ ፀብ በማስነሳት፣ በሰው አካልና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀል መከሰሳቸውን ቻርጁ ይገልጻል፡፡

መርማሪ ፖሊስ 1ኛ እና 2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ እንዲሁም 5ኛ ተከሳሾች የፈጸሙትን ወንጀል በመዘርዘር ክስ መርስቶባቸዋል፡፡

በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተፈጠረ ስለተባለው ረብሻ ያነጋገርናቸው የአዲሱ ካምፓስ የተማሪዎች አገልግሎት የሥራ ሒደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ደንደና የገለጹልን ደረሰ ከተባለው ረብሻ ጋር የማይገናኝና ለየት የለ ነገር ነው፡፡

እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፣ ከ15 ቀናት በፊት የሁለተኛ ዓመት የታሪክ ተማሪ የነበረች ብዙነሽ ብርሃኑ የምትባል ልጅ ትጠፋለች፡፡ ተማሪዎቹ ‹‹የት ሄደች?›› በሚል ዩኒቨርሲቲው በማፈላለግ ሥራው ላይ እንዲሰማራ ያዛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የቻለውን ሁሉ ቢያደርግም ተማሪዋ ልትገኝ አልቻለችም፡፡

በዚህ ጊዜ ተማሪዎቹ ‹‹እኛስ ምን ዋስትና አለን?›› በማለት ለመረበሽ ቢሞክሩም፣ ዩኒቨርሲቲው አረጋግቶ ትምህርት እንዲቀጥል ማድረጉን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ካምፓሶች መካከል (500 ሜትር ይራራቃሉ) አንድ ድልድይ መኖሩንና በሥሩ ትልቅ ባህር እንዳለ የገለጹት አስተባባሪው፣ የሕይወት አድን ሠራተኞች ቀጥረው ቢያስፈልጉም ብዙነሽ አልተገኘችም፡፡

በመጨረሻ በተደረገ ማፈላለግ በሕክምና መስጫ አካባቢ መታየቷን በጓደኞቿ በኩል በመጠቆሙ፣ የተባለው ጣቢያ ሄደው ሲጠይቁ፣ ልጅቷ ስትመረመር መፀነሷ ተነግሯት እንደሄደች እንደተገለጸላቸውና እስካሁን እንዳልተገኘች አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹም እስካሁን ስለሷ በማሰብ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሁለቱም ካምፓሶች 8362 ተማሪዎች መኖራቸውንም አቶ ብርሃኑ አሳውቀዋል፡፡

ኅዳር 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ተፈጠረ የተባለውን ረብሻ በሚመለከት ግን የተማሪዎች እርስ በርስ ግጭት በመሆኑ ‹‹ቀላል ነው›› ቢሉም ጉዳዩ ግን ተካሮ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቷል፡፡

ክስ የተመሠረተባቸውና በእስር ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ግን የሚያነሱት ቅሬታ አላቸው፡፡ ‹‹በሕግ ተደንግጐ የሚኘውን አንድ ሰው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋለ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት›› የሚለውን በመጣስ መብታቸውን ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለስድስት ቀናት ያህል ፖሊስ ጣቢያ ሲታሰሩም ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡም ወላጆቻቸው ተናግረዋል፡፡ መብታቸው ስለተጣሰም ለክልሉ መንግሥት እንደሚከሱም ገልጸዋል፡፡

የዲላ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ንጉሴ ዲዶ ደግሞ እንደገለጹት፣ በወቅቱና በሕጉ መሠረት የተያዙት በሙሉ ዲላ ከተማ የመመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር