ሙስና በአዲስ አበባ በኔትወርክ በመያያዙ ከኢሕአዴግ በስተቀር የሚፈታው እንደሌለ ተነገረ
- ተመዘገበ የተባለው የባለሥልጣናት ሀብት ይፋ እንዲደረግ ተጠየቀ ‹‹በየስብሰባው እየተወዳደሱና በጭብጨባ እየተደጋገፉ መለያየት ይቁም›› የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ድረስ በኔትወርክ የተያያዙ በመሆናቸው ሊፈታቸውም ሆነ ሊያስቆማቸው የሚችለው ‹‹ድርጅቱ›› ኢሕአዴግ ብቻ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ለግማሽ ቀን አዘጋጅቶት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ የሁሉም ክፍላተ ከተሞች፣ ወረዳዎች ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ነበር፡፡ ተሳታፊዎቹ እንደተናገሩት የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በመጠናቀቅ ላይ ካለው መስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ሊባል በሚችል ሁኔታ ከግንባታ፣ ከመሬትና ቤቶች ጋር በተገናኘ ነዋሪዎች እያለቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የመድረኩ ተሳታፊዎች በተለይ በአዲሱ የሥራ ዘመን ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ ያወቁ፣ የጠረጠሩና ሹክሹክታ የሰሙ የክፍላተ ከተሞችና የወረዳዎች ተሿሚዎች ‹‹የሚፈርስ የማይፈርስ፣ መንገድ የሚወጣበት የማይወጣበት፣ ክርክር ያለበት የሌለበት፣ ግንባታ የተፈቀደለት ያልተፈቀደለት…›› በማለት በሥራ ሰዓትና ከሥራ ውጪ የነዋሪዎችን ግድግዳና የውጭ በር ቀለም ሲቀቡ እንደሚውሉ ጠቁመዋል፡፡ ያለምንም ማስጠንቀቂያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡን ሰላም እየነሳው በመሆኑ፣ የአስተዳደሩና የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ትኩረት ሰጥተው ሊያስቆሟቸው ወይም ዕርምጃ ሊወስዱባቸው እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ አሳስበዋ