ሁለት ወራት የቀሩት ምርጫና የፓርቲዎቹ የቅስቀሳ ዘመቻ
ከ ሪፖርተር ጋዜጣ አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ልክ የዛሬ ሁለት ወር በመላው አገሪቱ ይከናወናል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ምዝገባ፣ የመራጮች ምዝገባና የመሳሰሉት ጉዳዮች ተፈጽመዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴም በይፋ ተጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሌላው የጊዜ ሰሌዳው አካል ነው፡፡ ከየካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. አንስቶ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የፓርቲዎችና የዕጩዎች የምርጫ ውድድር የተለያዩ ገጽታዎች ነው ያሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ባወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ ድልድል መሠረት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉዋቸውን የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጮችን የተመለከቱ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዲያስተላልፉ የተሰጠው አሠራር አንዱ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተሰጣቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ ዓምድ ድልድል በአግባቡ እየተጠቀሙበት እንዳልሆነ የሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ የተወሰኑ ፓርቲዎች እንዲሁ ልናስተላልፍ ያቀረብነው የቅስቀሳ ጽሑፍ ወይም ፕሮግራም አላግባብ ሳንሱር እየተደረገ ውድቅ ሆኖብናል በማለት መልሰው ይከሳሉ፡፡ በሁለቱ ጽንፎች መካከል እየተካሄደ ባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት፣ ፓርቲዎቹ ለሕዝብ የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሞቅ ባለ ሁኔታ በየከተማው የተለያዩ ሥፍራዎች የሚከናወኑ የምረጡኝ ዘመቻዎችና እንቅስቃሴዎች ግን እምብዛም የሚስተዋሉ አልሆኑም፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ይህን መሰሉ እንቅስቃሴ ከምርጫ 97 ጋር አብሮ መጥፋቱን ያወሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ፓርቲዎች ከምረጡኝ ቅስቀሳና ዘመቻ በተጨማሪ፣