ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በአምስት ኤክስፖርተሮች ላይ ዕርምጃ ወስጃለሁ አለ ቡና አቅራቢዎች ቡናቸውን ለኤክስፖርተሮች ሲያቀርቡ ክፍያ በትክክለኛው መንገድ ስለማይፈጸምላቸውና ከባንኮች ብድር በአግባቡ ስለማያገኙ፣ ከገበያ ለመውጣት መገደዳቸውን ተናገሩ፡፡ ቡና አቅራቢዎቹ ይህንን የተናገሩት ዓርብ የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን፣ የ‹‹ቀጥታ የገበያ ትስስር››ን ወይም (ቨርቲካል ኢንተግሬሽን)ን በተመለከተ ከአርሶ አደሮችና ከቡና አቅራቢዎች ጋር ውይይት ሲያካሂዱ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ቡና አቅራቢዎች ንብረታቸውን አስይዘው ከአርሶ አደሩ ቡና ከገዙ በኋላ ለኤክስፖርተሮች በሚሸጡበት ጊዜ፣ ኤክስፖርተሮች ‹‹የሸጣችሁልን ቡና የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያስቀመጠውን መሥፈርት አላሟላም›› በማለት ዓመቱ ሙሉ ገንዘባቸውን ይዞ እንደሚያንገላቷቸው የጅማ ዞን ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ናስር አብዱ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት ቡና አቅራቢዎች ለኤክስፖርተሮች ቡናቸውን በመሸጥ ይተዳደሩ እንደነበር፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ባወጣው ደንብ ቡና አቅራቢዎችም ሆኑ አርሶ አደሮች ቡናቸውን በቀጥታ ኤክስፖርት ማድረግ መቻላቸውን ገልጸው፣ ዘንድሮ በቀጥታ ቡና በመላክ 2.5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል በተወሰኑ ኤክስፖርተሮች የቡና ግብይት በሞኖፖሊ በመያዙ ቡና አቅራቢዎች ብዙ ጊዜ የውጭ ገበያ ሰንሰለቱ ላይ ችግር እንደሚገጥማቸው የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ቡና አቅራቢዎች በቀጥታ የገበያ ትስስር ከውጭ ገዥዎች ጋር የሚገናኙበት ሁኔታን መንግሥት መፍጠር አለበት ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ኤክስፖርተሮች የውጭ አገር ፈቃድ በማውጣት በሕገወጥ መንገድ ቡና እንደሚሸ