የአፍሪካ መሪዎች በአሜሪካ
ፎቶ ከ ሪፖርተር ጋዜጣ ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ያላት ንግድና ኢንቨስትመንት ለአሜሪካ ራስ ምታት እንደሆነ ይነገራል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ለምታደርገው ዕርዳታም ሆነ ኢንቨስትመንት ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ጀምሮ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች፡፡ ኩባንያዎቿም በአፍሪካ ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት ስለ ደኅንነት፣ ፀጥታና ሰላም ብሎም በአገሪቱ ስላለው የሠራተኛ አያያዝ መብት በቅድሚያ መወያየት ይፈልጋሉ፡፡ ቻይና ደግሞ በምትሠራባቸው አገሮች የውስጥ ጉዳይ እጇን አታስገባም፣ አትጠይቅም፡፡ ትኩረቷ ያለው ኢንቨስትመንቷ ላይ ነው፡፡ በዚህም ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ተመቻችታለች፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፍ በአፍሪካ መሠረቷን ጥላለች፣ ተጠናክራለች፡፡ የአፍሪካ መሪዎችንና የንግድ ማኅረሰብ አባላትን ሲያሻት በተናጠል፣ ሲያሻት በቡድን እያወያየች በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች በጋራና በተናጠል ትሠራለች፡፡ ብድር ለመስጠትም የምትሰጠውን አገር የውስጥ ጉዳይ ከቅድመ ሁኔታ ወይም ከመደራደሪያ ውስጥ አታስገባውም፡፡ በመሆኑም በአፍሪካ ውስጥ ከአሜሪካ በበለጠ ሰፊ ድርሻ ይዛ ትሠራለች፡፡ ቻይና ለአፍሪካ የምትልከውም ሆነ ከፍሪካ ወደ አገሯ የምታስገባው አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ካላት ሲነፃፀር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በመሆኑም አሜሪካ በቻይና እጅ ከገባው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት መቋደስና በአፍሪካ ውስጥም መኖሯን ማሳወቅ ትፈልጋለች፡፡ በመሆኑም አሜሪካ ከዚህ በፊት አድርጋ የማታውቀውን የአሜሪካና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ እያካሄደች ነው፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ በተጀመረውና ረቡዕ በሚያበቃው የአሜሪካና የአፍሪካ መሪዎች