ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ ተመረጠች
- ውድድሩ አፍሪካና አውሮፓን አፎካክሯል በዓለም አቀፍ የቡና ግብይት ውስጥ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱት ቡና ገዥ ኩባንያዎችና አምራቾች በአባልነት የታቀፉበት ዓለም አቀፍ የቡና ድርጅት፣ ኢትዮጵያ አራተኛውን ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ መረጠ፡፡ እ.ኤ.አ. በማርች 2016 የሚዘጋጀውን ኮንፈረንስ ለማስተናገድ የመጨረሻው ውድድር ላይ ቀርበው የነበሩት ኢትዮጵያና ጣሊያን ናቸው፡፡ ምርጫው በተካሄደበት ለንደን ከተማ ተገኝተው የነበሩ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት እንደገለጹት፣ ውድድሩ ከፍተኛ ፉክክር የነበረበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ልታሸንፍ ችላለች፡፡ በመጨረሻው ውድድር ላይ ከድምፅ ሰጪዎች መካከል ግዙፎቹ የአውሮፓ ቡና ገዥ ኩባንያዎች ድምፃቸውን ለጣሊያን ሰጥተው ነበር፡፡ አፍሪካውያንና ሌሎች ቡና አብቃዮች ደግሞ ለኢትዮጵያ ድምፅ በመስጠት ውድድሩ በአፍሪካውያንና በአውሮፓውያን መካከል እንዲሆን አድርገው ነበር ብለዋል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፉ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ድምፅ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው ብራዚል ድምጿን ለኢትዮጵያ በመስጠቷ ለኢትዮጵያ አሸናፊነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፡፡ ከመጨረሻው ውድድር ቀደም ብሎ ኮንፈረንሱን ለማዘጋጀት ከአፍሪካ ኮትዲቯር፣ ጋቦንና ኬንያ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም ሁሉም አገሮች የኢትዮጵያን የተወዳዳሪነት ጥያቄ በመቀበል ድምፃቸውን ሰጥተዋታል፡፡ ኮንፈረንሱ አፍሪካ ውስጥ መካሄዱ ትልቅ ዕድል ነው በማለት ለኢትዮጵያ ዕድሉ እንዲሰጣት አፍሪካውያኑ ድጋፍ እንዳሰባሰቡም በቦታው ከነበሩ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዓለም የቡና ድርጅት (አይሲኦ) መካከል 50 በመቶዎቹ የቡና ገዥ ኩባንያዎች የሚወከሉባቸው አገሮች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ቡና አምራች አገሮች