የሰሞኑ ዝናብ ያልተለመደ ነው
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 28 ፣ 2006 ( ኤፍ.ቢ.ሲ ) የብሄራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት በመስከረም ወር እየጣለ ያለው ዝናብ ያልተለመደ መሆኑን ገለጸ ። በኤጀንሲው የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ድሪባ ቆሪቻ እንደገለጹት ፥ ከባለፈው መስከረም 20 ጀምሮ አብዛኛውን የሃገሪቱን ክፍል የሸፈነ የዝናብ ስርጭት ተስተውሏል። ዳይሬክተሩ በተለይም በአማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ ደቡብና ሃረሪ ክልሎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሰሜናዊ አጋማሽ ድሬዳዋን ጨምሮ ይህ ያልተለመደ ዝናብ ያለማቋረጥ መዝነቡን እና በተለይም የአማራ መካከለኛው ምስራቅ ፣ ደቡብ ኦሮሚያ እና የደቡብ ክልል ሰሜናዊ አጋማሽ ከበድ ያለ ዝናብን ያስተናገዱ አካባቢዎች እንደነበሩ ገልጸዋል ። ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ግን ይህ የዝናብ ስርጭት በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍለ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን ነው አቶ ድሪባ የተናገሩት ። በተመሳሳይ በቀጣዮቹ አራት ቀናት ውስጥ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑትና በዚህ ወቅት ሰብል መሰብሰብ በሚጀምሩት የሃገሪቱ ሰሜን ፣ ሰሜን ምስራቅና የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ እንደሚቀንስ አቶ ድሪባ አስረድተዋል ። የሜትዮሮሎጂ ትንበያ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሃገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ የዝናብ ስርጭቱ በመጠንም ሆነ በሽፋን እየተስፋፋ እንደሚሄድ ይጠበቃል ። ከዚህ ጋር በተያያዘ የወቅቱ ዝናብ ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች ጥቅም ሊኖረው እንደሚችል ነው ሀላፊው የገለጹት። በቀጣይ ግን እንደባለፈው ሳምንት የተስፋፋ ዝናብ እንደማይጠበቅ ፥ ይሁንና በአንዳንድ ስፍራዎች ያልተጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ረገድ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲወስድ አሳስበዋል።