ሕዝብ ‹‹መልካም አስተዳደር በተግባር!›› እያለ ነው
መንግሥት መልካም አስተዳደር መኖር አለበት ይላል ወይ? አዎን! ኢሕአዴግም በጉባዔው ብሏል፣ በውሳኔም አሳልፏል፡፡ በየቀኑ መግለጫ ይሰጥበታል፡፡ መልካም አስተዳደር እውን የማታደርጉ ወዮላችሁ ብሏል፡፡ የመልካም አስተዳደር አለመኖር አደጋንም ገልጿል፡፡ መንግሥትም ብሏል፣ ኢሕአዴግም ብሏል፣ ሕዝብም ሰምቷል፣ አዳምጧል፡፡ ጥያቄው የተባለው፣ የተወሰነውና ቃል የተገባው መልካም አስተዳደር የት አለ የሚል ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ‹‹መልካም አስተዳደር በተግባር!›› ነውና፡፡ በተግባር ያልታየ ነገር ‹‹ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ›› ነውና፡፡ መንግሥት በፌዴራል ደረጃም በክልል ደረጃም ወደ ተጨባጭና አሳማኝ ተግባር ይግባ፡፡ ይናገር ሳይሆን ያሳይ፡፡ በዚህ መሥሪያ ቤት ሕዝቡ መልካም አስተዳደር አላገኘም ከተባለ መንግሥት ያንን መሥሪያ ቤት ገባ ብሎ መመርመርና መፈተሽ አለበት፡፡ በመልካም አስተዳደር መጥፋት ምክንያት ያላግባብና ከሕግ ውጭ የተሰጠ ጥቅም ካለ ውሳኔው ትክክል አልነበረም በማለት፣ የወሰኑት ሰዎችም መጠየቅ አለባቸው ብሎ የማስተካከያና የእርምት ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በመልካም አስተዳደር ምክንያት በደል የደረሰባቸው ዜጎች ካሉ ፈትሾ ያላግባብና ከሕግ ውጭ መብታቸው ተጥሷል፣ ተጎድተዋል በማለት የደረሰባቸው በደል እንዳይቀጥል አስተካክሎ፣ አርሞና ይቅርታ ጠይቆ ትክክለኛ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ያኔ ነው ሕዝብ እውነትም መልካም አስተዳደር አለ የሚለው፡፡ እውነትም ለመልካም አስተዳደር ከልብ ቆሟል ብሎ ሕዝብ የሚያምነውና ከጎኑ የሚቆመው፡፡ ስለዚህ ተግባር! ተግባር! አሁንም ተግባር! መንግሥት ለመልካም አስተዳደር መስፈን እንቅስቃሴ ሲያደርግ ሥራው ቀላልና ፈጣን ይሆንለታል ማለት አይደለም፡፡ ሴረኛ ያደናቅፈዋል፡፡ ሙሰኛና ፀረ መልካም