በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ላለፉት ሦስት ዓመታት በአዲስ አበባ የቆዩት አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ በእስልምና ተከታዮችና በመንግሥት መካከል ስላለው አለመግባባት፣ በዓባይ ወንዝና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ስላለው ፖለቲካዊ ትኩሳትና ሌሎች ጉዳዮች የመንግሥታቸውን አቋምና የራሳቸውን ግንዛቤ ለሪፖርተር ጋዜጣና ሌሎች ሁለት ሚዲያዎች ባለፈው ሰኞ አካፍለዋል፡፡ አምባሳደሩ የሦስት ዓመታት የአዲስ አበባ ተልኳቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል በእስልምና ተከታዮችና በመንግሥት መካከል የሚስተዋለው አለመግባባትና ግጭት አንዱ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮችና ሃይማኖቶች የሚኖሩባት አገር ነች፡፡ ይህ ስብጥር እንደረጋ እንዲቆይ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የእምነት ነፃነትና እኩልነትን አረጋግጧል፤›› በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት አምባሳደር ቡዝ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ እንዲሁም ሃይማኖቶች በመንግሥት ላይ ጣልቃ እንዳይገቡ በግልጽ በሕገ መንግሥቱ መቀመጡ መሠረታዊ ነው ይላሉ፡፡ ይህ መሆኑ የትኛውም ሃይማኖት ነፃነት እንዲኖረውና ለተከታዮቹም የመረጡትን ሃይማኖት የመከተል መብት ይሰጣል ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ካለው ሁኔታ የምንረዳው ግን አንዳንድ ሰዎች ይህንን የመቀየርና የራሳቸውን እምነት በሌሎች ላይ በግድ የመጫን ፍላጎትና አመለካከት መኖሩን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ወይም አክራሪነት ሊባል ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እየጣረ ያለውም ይህንን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ነው፡፡ ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነት ፅንሰ ሐሳብ የሚጎዳና በአገሪቱ የቆየውን የሃይማኖት ብዝኃነት የሚያደፈርስ በመሆኑ ነው፤›› በማለት ይገልጻ