የሲዳማ ብሔር ተወላጅ የሆኑት አቶ ደሴ በቅርቡ የትምህርት ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙት ከቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ላይ የክልሉን መንግሥት ኃላፊነት ተረክበዋል፡፡ አቶ ደሴ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማዕከል የሆነውን የደቡብ ክልል ኃላፊነት ሲረከቡ እንደተናገሩት፣ ለሕዝቡ እኩል የልማት ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ የክልሉን ሕዝብ አንድነት ለማጠናከርና የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ምንም እንኳን በክልሉ ሴክተር መሥርያ ቤቶች ከዚህ ቀደም ባይሠሩም፣ ከ1996 ዓ.ም እስከ 1998 ዓ.ም የይርጋ ዓለም ከተማ ከንቲባ፣ ከ1998 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ትምህርት መምርያ ኃላፊ፣ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ማገልገላቸው ታውቋል፡፡ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ሰኔ ወር ድረስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆን የሠሩ ሲሆን፣ ከሐምሌ 6 ቀን ጀምሮ አዲሱን ኃላፊነታቸውን ተረክበዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ በባይሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በለውጥ አመራር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ደሴ፣ በአዲሱ ሹመት የተሻለ ለውጥ ያስመዘግባሉ ተብሎ እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በዞን ደረጃም ሆነ በፌደራል ደረጃ የነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ለዚህ ኃላፊነት እንዳበቃቸው በክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ከተሳታፉ ግለሰቦች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡ “አቶ ደሴ በተለይ በሲዳማ ዞን አስተዳዳሪነታቸው ወቅት ባሳዩት አመራር የተነሳ ክልሉን በፍትሐዊነት ያስተዳድራሉ ተብሎ ይጠበቃል፤” ሲሉ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን ለሪፖር