ጫፍ ፍቅር ሀይቅ ጋ ወራጅ አለ!
አዲስ አበባ የምር ናፍቃኛለች፡፡ ልክ ፍቅረኛውን ፒያሣ መሀሙድ ጋር እንደቀጠረ ጐረምሳ፡፡ እኔ አዋሳ ነው ያለሁት፡፡ አዋሳ ደግሞ ሙቀት አለ፡፡ ሙቀት ስላችሁ የፀሐይ እንዳይመስላችሁ፡፡ የመሬት ሙስና የወለደው የፖለቲካ ሙቀት እንጂ፡፡ እሳት እንደነካው ፌስታል አንጀት የሚያኮማትር ትኩሳት! እንጨት እንደወጋው የፊት ቁስል ሆድ የሚያሳምም ወላፈን! ቀጣዩ በረሀ ወለድ ሃሜት ግን ጭራሽኑ ተስፋ አስቆረጠኝ፡፡ የፌደራሉ መንግስት ሀዋሳን እንደ ማደጐ ልጅ ወስዶ በሞግዚትነት ሊያሳድጋት ነው፡፡ አላመንኩም፤ አይደረግም ብዬም ልጮህ ነበር፡፡ አላደረኩትም፡፡ የመንግስቴን ሰምና ወርቅ ፀባይ አውቀዋለሁ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ሽፈራው ሽጉጤ “የሆነ በሬ ወለደ ዓይነት የኪራይ ሰብሳቢዎች አሉባልታ” ሲሉ ጭንቀቴ ላይ ቀዝቃዛ ልማታዊ ውሀ አፈሰሱበት፡፡ አዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁሽ… ይገባኛል፡፡ ከአዱ ገነት መውጣት ያስጨንቃል፡፡ መራቅ ያስፈራል፡፡ መሸሽ ሆድ ያባባል፡፡ ደግሞስ ወዴት ይኬዳል? የክፍለ ሀገራት ቅጥ ያጣ የዘውጌ ፖለቲካ፣ ወንዝ የማያሻግር የሠፈር ኢኮኖሚ እና ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤያቸው አንገት ያስደፋል፡፡ በዚያ ላይ ባቅላባ የላቸውም፡፡ የኛ ዓላማ ግን አዋሳን መውረር ነውና የምግብ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፡፡ ታጋይ ሆዳም ነው እንዴ? የመሀል ሠፈሪ ልጆች አዲስ ከተማ ት/ቤት ጐን ካለው መነሀርያ ትኬት መቁረጥ ትችላላችሁ፡፡ ከሳሪስ በታች ወይም የጥጉ መደብ ባለቤቶች፡፡ ከአዲሱ የቃሊቲ መነሀሪያም የአዋሳን “በሮ ገዳይ” ሚኒባሶች ታገኛላችሁ፡፡ ዕቃ እንዳትረሱ፡፡ መታወቂያ ካሜራ፣ ደብተር፣ ብዕር፣ እርሳስ፡፡ ት/ቤት የምንሄድ አስመሰልኩት እንዴ? በፍፁም! አዋሳ ለሚቆዝም፣ ለሚያዜም፣ ለሚጽፍና ለሞንጭሮ አደር ተመራጭ ናት፡፡