በደቡብ ክልል አዲሱ የሊዝ አዋጅ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል -የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር
በደቡብ ክልል አዲሱ የሊዝ አዋጅ ከዛሬ ጀምሮ በየደረጃው ተግባራዊ እንደሚሆን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የንግድ ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ሀላፊ አስታወቁ ። በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ህብረተሰቡም ለአዋጁ ተግባራዊነት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የቢሮው ሃላፊ አቶ ታገሰ ጫፎ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በሀገር ደረጃ ህዳር 18/2004 የጸደቀው አዲሱ የሊዝ አዋጅ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ መሬት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዘቦች የጋራ ሀብት እንደመሆኑ የከተማ ቦታ በሊዝ ጨረታ ወስዶ ያለማ ሰው እሴት እንደሚፈጥርለትና ተጠቃሚ እንደሚሆን አስታዉቀዋል ። በአዋጁ መሰረት የተከለከለው ባዶ መሬት በሊዝ ከወሰደ በኋላ ሳይሰራበት መሬቱን አሲዞ አለአግባብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ከባንክ መበደርና መሸጥ ነው ብለዋል፡፡ መሬት ልማታዊ ባልሆነ መንገድ ወስዶ በአቋራጭ መበልጸግና ሀብት ማግበስበስ እንደማይቻል በአዋጁ ላይ በግልጽ መደንገጉን ያስረዱት አቶ ታገሰ በዚህ ዐይነት ህገ ወጥ አካሄድ የመሬት ዋጋ ጣሪያ ከመድረሱም በላይ ለልማት የሚውለው ገንዘብ በመሬት ግዥና ሽያጭ እየባከነ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ የመሬት አስተዳደር ስርዓትና የመሬት አቅርቦትን ከከራይ ሰብሳቢነት የጸዳ ለማድረግ አዋጁ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመልከተው በፕላን መሰረት ቤት የሰራና በዙሪያው ያለማውን ሀብት መሸጥ እንደሚችል ፣ ነገር ግን መሰረት በመጣልና ከ50 በመቶ በታች ግንባታ በማካሄድ በከፍተኛ ገንዘብ መሸጥ የማይቻል መሆኑን ህዝቡ በግልጽ መገንዘብ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ነባር ይዞታዎች በውርስ ማስተላላፍ እንጂ ወደ ሊዝ የሚገባን መሬት ለሶስተኛ ወገን