የሕገ መንግሥታት ያላቻ ንፅፅርና የኢ-ዘላቂነት ዳንኪራ
በበሪሁ ተወልደ ብርሃን አንድን ነገር ከመጻፌ በፊት ራሴን እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ መጻፌ ጥቅም ይኖረው ይሆን? የምጽፈው ነገር ምክንያታዊ ነውን? ይህ ካልሆነ ግን ዝምታን እመርጣለሁ፡፡ ዛሬ ለመጻፍ ስነሳም ለጥያቄዎቼ በቂ ምላሽ ከሰጠሁ በኋላ ነው፡፡ ሪፖርተር ጋዜጣ በሐምሌ 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ዕትሙ በአገራችን ዕውቅ ከሆኑ የሕግ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም በማስታከክ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ሕመም ቢያጋጥመው ማን ተክቶት ይሠራል ለሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ክፍተት አለበት›› በሚል ርዕስ የቀረበውን ጽሑፍ አንብቤ የተነሳው ጭብጥ፣ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ብዙም ባላምንበትም፣ በተነሱት አንዳንድ ሐሳቦች ላይ ከተነሱት ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችና ድንጋጌዎች ምክንያታዊ እሳቤ (rationale)፣ ይዘት (content)፣ መልእክት (message)፣ ትርጓሜ (interpretation) እና ማብራርያ ምሳሌዎች (illusturation) ረገድ የምስማማባቸውን ትቼ፣ በማልስማማባቸው ሐሳቦች ላይ ይን መጣጥፍ ስጭር፣ በተነሱት ጉዳዮች ላይ ምላሽ ለመስጠትና ለእሰጥ አገባ በር ለመክፈት እንዳልሆነና በሠለጠነው ሐሳብ የማንሸራሸር ውቅያኖስ ላይ ጠበል ጠዲቅ ከመቃመስ አኳያ ብቻና ብቻ እንደሆነ ግንዛቤ እንዲወሰድበት እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት፣ ሕገ መንግሥት ከሌሎች ሕጎች የሚለይበት መሠረታዊ ባሕርያት፣ የፓርላማ ሥርዓትና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን መሠረታዊ መገለጫዎችና ከፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የሚመሳሰሉበትና የሚለያዩበት ሁኔታ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ማዕቀፍ፣ ሕገ መንግሥታዊ ክፍተትና የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰያየምና ያንፀባረቀው አቋም፣ እንደ መንደርደርያነት በመመልከት