በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ምደባ ወደ ፖለቲከኞች እያዘነበለ ነውን?
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለትችት ከዳረጓቸው ጉዳዮች መካከል የአሜሪካ የውጭ ዲፕሎማሲ ሥራ ላይ የሚመድቧቸው ሰዎች ማንነት አንዱ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ እ.ኤ.አ. በ2012 ለድጋሚ ፕሬዚዳንትነት በተወዳደሩበት ወቅት ለቅስቀሳ ከፍተኛ ገንዘብ ሲያሰባስቡ የነበሩ ግለሰቦች ፕሬዚዳንት ኦባማ በድጋሚ ወንበራቸውን ካገኙ በኋላ የተወሰኑት በተለያዩ አገሮች በአምባሳደርነትና በዲፕሎማትነት ተመድበዋል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በአምባሳደርነት የተመደበው ማቲው ባርዙን ለፕሬዚዳንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ወጪ ከተሰበሰበው 700 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 2.3 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነውን በግሉ አሰባስቧል፡፡ በተመሳሳይ ጆን ፊሊፕስ ለኦባማ የምርጫ ዘመቻ 500 ሺሕ ዶላር ከሰበሰበ በኋላ በጣሊያን ሮም የአሜሪካ ዲፕሎማት ሆኖ ተመድቧል፡፡ ጆን ኤመርሰን 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያሰባሰበ ሲሆን፣ የተመደበው ጀርመን በሚገኘው ኤምባሲ ነው፡፡ ጄን ስቴትሰን 2.4 ሚሊዮን ዶላር አሰባስቦ፣ የተመደበው በፈረንሳይ ፓሪስ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአሜሪካ ፕሮፌሽናል ዲፕሎማቶች ማኅበርና ጡረታ የወጡ የአገሪቱ አምባሳደሮች የፕሬዚዳንት ኦባማን ድርጊት ከመውቀስ አልፈው ‹‹የመንግሥት ቢሮን የመሸጥ ያህል ነው›› በማለት ድርጊቱን ተችተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ የፈጠጠ የጥቅም ግንኙነት ያለበት የውጭ ዲፕሎማቶች አመዳደብ በኢትዮጵያ ባይስተዋልም የግለሰቦችን ነፃነት የሚጋፋ አካሄድና በሕግ የማይመራ አመዳደብ ለበርካታ ዓመታት ሥር ሰዶ የከረመ እንደነበር የተወሰኑ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ፡፡ በተለይ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ፈተና ውስጥ ገብቶ የነበረ መሆኑን የተገነዘበው ገዥው ፓርቲ ከገባበት አጣብቂኝ ከወጣ በኋላ የአባላቱን ቁጥር ለማ