ይቅርታ መጠየቅ ተጠያቂነትን ያስቀራልን

በእርግጥ፣ በሲዳማ ውስጥ ባለፉት ሰባት ዓመታት ትልቅ የፖለቲካና የማኅበራዊ ለውጥ ተከስቷል። በዚህ የሰባት ዓመት የቀድሞ አመራር ዘመን የተነሱ የሥራ ዕድል፣ የፍትሕ፣ የተሳትፎና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ አግኝተዋል ወይስ አላገኙም የሚለው እንደየአተያዩ ሊለያይ ይችላል። ነገር ግን ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች ሊስማሙበት የሚችሉት አንድ ጉዳይ ቢኖር፣ ከመልካም አስተዳደር አንፃር የታዩ እና የክልሉን የዲሞክራሲያዊ እድገት ያደናቀፉ አሰራሮች፣ ሕዝባዊ ጥያቄዎችን የማፈን፣ የመናቅ እና አሳንሶ የማየት አባዜ የአመራሩ ባህል ሆኖ መቆየቱ ነው። በዚህም ሕዝቡ ቅሬታውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቷል፤ ሰሚ ባያገኝም።

በዚህ አውድ፣ እኚህ የቀድሞ አመራር ሥልጣናቸውን ሲለቁ ከሕዝብ ይቅርታ መጠየቃቸው በራሱ አንድ አዎንታዊ የሞራል እርምጃ ሊሆን ይችላል። ግን ይቅርታ መጠየቅ ተጠያቂነትን አያስቀርም። በተቃራኒው፣ እውነተኛ ይቅርታ ወደ ተጠያቂነት የሚወስድ መነሻ መንገድ መሆን አለበት።
ይቅርታ እና ተጠያቂነት አንድ ነገር አይደሉም። ይቅርታ ጸጸትን መግለጽ ሲሆን፣ ተጠያቂነት ግን ምን እንደተፈጠረ፣ ለምን እንደተፈጠረ እና የማን ኃላፊነት እንደነበረ በማስረጃ መመርመር ነው። ሕግ የተጣሰበት ጉዳይ ካለም፣ ይቅርታ የሕግን ሂደት ሊተካ አይችልም። ተጠያቂነት ማለት በቀል ሳይሆን፣ እውነትን መፈለግና ፍትሕን ማረጋገጥ ነው።

በሲዳማ ውስጥ የወጣቶች ድምፅ እና ጥያቄ በተለይ ትኩረት ይፈልጋል። ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ጥያቄና ቅሬታቸውን መግለጻቸው ችግርን በራሱ አይፈታም፤ ነገር ግን ድምፃቸውን የማሰማት አንዱ መንገድ ነው። እኚ አመራሪ፣ በአመራር ጊዜያቸው ወጣቶች በፌስቡክ ላይ የሚጽፉትን ጥያቄና ቅሬታ “ምንም ነገር አያመጣም” በሚል አመለካከት መመልከታቸው፣ እና ዛሬ ይቅርታ ከመጠየቅ ጋር ሲታይ፣ የሕዝብ ድምፅን መስማትና ተቃውሞን መቀበል በአመራር ውስጥ ምን ቦታ ነበረው? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።

እዚህ ላይ ጉዳዩን ወደ የግል ክስ መቀየር አያስፈልግም። ዋናው ጉዳይ የአንድ ግለሰብ ስም ሳይሆን፣ በሰባት ዓመታት የአመራር ዘመን የነበረውን አሰራር፣ ውሳኔና ለሕዝብ ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ በተጨባጭ መመርመር ነው። ማን ምን አደረገ? ምን ሊደረግ ይችል ነበር? የተፈጠሩ ችግሮችስ ለምን ተፈጠሩ? እነዚህ ጥያቄዎች ከቁጣ ይልቅ ለሲዳማ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት የሚያግዙ ናቸው።

ወጣም ወረደም፣ ይቅርታ ሊያስታርቅ ይችላል፤ ግን ተጠያቂነትን ሊያስቀር አይችልም። ሲዳማ የሚፈልገው ያለፈውን መርሳት ሳይሆን፣ ካለፈው በመማር የተሻለ አመራርና የተሻለ የሕዝባዊ ግንኙነት መገንባት ነው። ይቅርታ የመጀመሪያው ደረጃ ከሆነ፣ እውነት፣ ፍትሕ እና ተጠያቂነት ደግሞ የሂደቱ ቀጣይ ደረጃዎች መሆን አለባቸው። እናንተስ ምን ትላላችሁ?

Comments

Popular posts from this blog

ስለከሸፈው “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ጥራዝ አንዳንድ ነጥቦች

SIDAMA Micro-Finance Institution

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት