ቅዱስ ጊዮርጊስና ሲዳማ ቡና ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ
አዲስ አበባ የካቲት 12/2006 በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በ11ኛው ሳምንት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን አጠናከረ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት ጨዋታውን ከሐዋሳ ከነማን ጋር አድርጎ 1ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፉ ከሌሎች ቡድኖች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ይበልጥ እያሰፋ ነው። በኃይሉ አሰፋ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቸኛዋንና ለአሸናፊነት ያበቃቻቸውን ግብ አስቆጥሯል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ በ 27 ነጥብ አንዱንም ሳይሸነፍ የሊጉን መሪነት እንደያዘ ነው። በሌላ በኩል ሲዳማ ቡናና ሙገር ሲሚንቶን በይርጋለም ላይ ባካሄዱት ጨዋታ ሲዳማ ቡና 2 ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።አሁን ላይ ሲዳማ ቡና 9 ነጥቦች ያሉት ሲሆን ይህን ጨዋታ በማሸነፉ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ችሏል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ ኡመድ ኡክሪ በ9 ጨዋታዋች 9 ጎሎች በማስቆጠር የፕሪሚሪ ሊጉን የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል።