የኢትዮጵያ ቡና ከዓለም ገበያ እየራቀ መሆኑ ሥጋት ፈጥሯል
የኢትዮጵያ ቡና ከዓለም አቀፍ ገበያ እየራቀ መጥቶ፣ ከነጭራሹ ሊወጣ የተቃረበበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝ ለዘርፉ ቅርብ የሆኑ ተዋንያዎች የሚስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዓለም ቡናን ያበረከተች አገር ከመሆኗ ባሻገር እጅግ ተወዳጅ የሆነ ቡና የምታመርት አገር ናት፡፡ ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች ይህንኑ የጣዕም ልዩነት በመረዳት የኢትዮጵያን ቡና ለመግዛት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ በቢሮክራሲ ውጥንቅጦች ምክንያት ቡናውን ማግኘት እንዳልቻሉ እየተናገሩ ነው፡፡ በቡና ግብይት ላይ ያለው ውጣ ውረድ ከፍተኛና ገዥዎች የማይተማመኑበት ደረጃ ላይ እየደረሰ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ በጣዕሙ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የኢትዮጵያ ቡና ዋጋ እያጣ መምጣቱ የሚያስቆጭ ወቅታዊ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የችግሩ ምንጮች በዋነኛነት የመንግሥት የቡና ግብይት አቀንቃኞቹ የንግድ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት እንደሆኑ የዘርፉ ተዋናዮች ያምናሉ፡፡ የቡና ግብይት ተዋናዮች እንደሚሉት፣ የችግሩ ምንጮች በእነዚህ ሁለት መንግሥታዊ ተቋማት የተወለዱ ችግሮች ናቸው፡፡ በመጀመሪያ የንግድ ሚኒስቴር የቡና ግብይት ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች የቡና ግብይት ሁኔታን በሚገባ አለመረዳታቸው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሥራ ኃላፊዎች የግብይት ሁኔታውን ቢያውቁም፣ የመወሰን አቅም የሌላቸው በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹እነዚህ አካላት ግን ያሉባቸውን የተወሰኑ ችግሮች ለማረም አልሞከሩም፤›› ይላሉ የተበሳጩት የቡና ግብይት ተዋናዮች፡፡ በምርት ገበያ በኩል አሉ ከሚባሉት ችግሮች መካከል አንዱ የቡና ልኬት (ሚዛን) ችግር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ባሉት ዓመታት በቡና ግዥ ሒደት የቡና ገለፋት በ20 በመቶ ታሳቢ ተደርጎ በግዥ ሒደት ቅናሽ ይደረግ ነበር፡፡ አሁን ባለው የምርት ገበያ