ሲዳማ ዞን “አስተዳዳሪ” ሚሊዮን ማቴዎስ ሐምሌ 04/2004 የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫን በተመለከተ ህዝቡ ያለውን ስሜት ለመግለጽ የተሰጠ መግለጫና አቅጣጫዎቻችን
ሲዳማ ህዝብ ክልል ለመሆን ያስተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ሰሞኑን የዞኑ “አስተዳዳሪ” ሚሊዮን ማቴዎስ በሐምሌ 04/2004 እትም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ደኢህዴን ጋዜጣ ላይ እንደወትሮው የጓዶቹ መግለጫዎችና ዜናዎች ሁሉ ንቀት የበዛበትና ተራ ስድብ ያዘለ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ የጋዜጣው ተነባቢነት ከሚገመተው በላይ መጥበቡና በአጠቃላይ በህዝብ ዘንድ እንኳንስ አሁን ባለንበት ሁኔታ ቀድሞውንም ቢሆን ተቀባይነት የለሌው ከመሆኑ የተነሳ ወደሰፊው ህዝብ ጆሮ መድረስ በነበረበት ፍጥነት በሰፊው ባይደርስም ከአጀንዳው አንገብጋቢነት አንጻር አሁን የመነጋገሪያ ርዕስ በመሆኑ ይሄንን ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ጋዜጣ በፊት ገጹ ላይ “የሐዋሳ ከተማ ነዋሪውን ህዝብ የሚወክል አመራር እንዲኖሩት የቀረበውን አቅጣጫ በመቃወም በቅርቡ የሐዋሳ ከተማ ተሸጠች የሚል ውዥምብር በመንዛት ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት ሲሯሯጡ የነበሩ ፀረ - ልማት ኃይሎች በመላው ህብረተሰብ ትብብርና በድርጅቱ የጠራ መስመር ሊከሽፍ ችሏል” በማለት የነበረውን የህዝብ ቁጣ “ውዥምብር” ብለው በማጣጣል እርሱም ቢሆን በሲዳማ ህዝብና በድርጅታቸው መክሸፉን አስነብበውናል፡፡ እዚህ ላይ ተቃውሞው መነሻ እንዳለው ካለመካዳቸውም በላይ በተቃውሞው የተሳተፉት እነርሱ እንደሚሉት “ፀረ - ልማት ኃሎች” ሳይሆኑ ሰፊው የሲዳማ ህዝብ መሆኑን “ውዥምብር” የሚለው ቃላቸው ያሳብቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ጥቂት “ፀረ - ልማት ኃሎች” “ውዥምብር” መፍጠር አይችሉምና፤ ሊፈጥሩ የሚችሉት ሹክሹክታ፣ ሀሜትና ጥቂት “ንፋስ” ነው፡፡ “ውዥምብር” ሊኖር የሚችለው ሃይለኛ የሆነ እንቅስቃሴና ተቃውሞ ሲኖር ነው፡፡ ይሄንንም እውነታ ለመግለጥ እየሞከርን ያለነው ከሲዳማ ውጭ ላሉ አንባቢያን