የኢጋድ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ መካኒዝም ድንበር ተሻጋሪ የሰላም ጉባዔ በሐዋሳ ይካሄዳል
ሐዋሳ ታህሳስ 4/2011 የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት/ኢጋድ/ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ መካኒዝም ድንበር ተሻጋሪ የሰላም ጉባዔውን ከነገ ጀምሮ በሐዋሳ ያካሂዳል፡፡ የኢጋድ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ መካኒዝም የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር ወይዘሮ ትዕግሥት ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያና በኬንያ ሰላምና ልማት ዙሪያ የሚያተኩረው ጉባዔ በከፍተኛ ኃላፊዎች ደረጃ ለሁለት ቀናት ይደረጋል፡፡ በቅርቡ በሞያሌና በጂንካ በኢትዮጵያና በኬንያ ማህበረሰቦች ደረጃ በተደረገው ውይይት የተነሱ ዓበይት ጉዳዮች የጉባዔው ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆኑና ውሳኔ እንደሚሰጥባቸው ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በሰላም ሚኒስትር ይመራል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ጉባዔ ላይ የኬንያ አቻቸውና የኢጋድ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የአገሮቹ ተወካዮች እንደሚሳተፉበት ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የሶማሌ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድርና ከኬንያ የቱርካናና የመርሳቤት አስተዳደሮች ከፍተኛ አመራሮች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ወይዘሮ ትዕግሥት ገልጸዋል፡፡ ምንጭ