ሐዋሳ ከተማ በ457 ሚሊዮን ብር የሚያስገነባው ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በከፊል አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሐዋሳ ከተማ በ457 ሚሊዮን ብር የሚያስገነባው ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በከፊል አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው፡፡ የኤርፖርት ግንባታው ከ14 ወራት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ ግንባታውን የሚያካሂደው አገር በቀል ኩባንያ የሆነው ዮቴክ ኮንስትራክሽን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ሦስት ኪሎ ሜትር የአውሮፕላን መንደርደሪያ፣ የአውሮፕላን መዞሪያ (Taxi way)፣ የአውሮፕላን ማቆሚያና የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ያካትታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዮቴክ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ፣ ማዞሪያና ማቆሚያ ግንባታውን በማካሄድ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድም፣ የፕሮጀክቱ 85 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ሦስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ካለው መንደርደሪያ ግንባታ ውስጥ ሁለት ኪሎ ሜትር መጠናቀቁን የተቀረው አንድ ኪሎ ሜትር በሁለት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያው እንደ ቦይንግ 777 ያሉ ግዙፍ አውሮፕላኖች ማሳረፍ የሚችል ሲሆን፣ ሁለት ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት በሁለት ዙር ለብሷል፡፡ የሁለት ኪሎ ሜትር ግንባታ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ በረራ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦምባርደየር ኪው 400 አውሮፕላኖች በተገቢው ሁኔታ መነሳትና ማረፍ እንደሚችሉ ተረጋግጧል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሃና አጥናፉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ወደ ሐዋሳ በሳምንት አራት ቀናት በኪው 400 አውሮፕላኖች የበረራ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ አየር መንገዱ ሚያዝያ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በረራውን ለመጀመር ማቀዱን ወ