ትኩረት ለእንሰት !
እንሰት በአብዛኛው የደቡብ ክልል ዞኖችና በተወሰኑ የኦሮሚያ አከባቢዎች የሚመረት ተወዳጅ የምግብ ተክል ከመሆኑም ባሻገር የህብረተሰቡ የክብር መገለጫም ተደርጎ ይወሰዳል። የጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሃዲያ፣ ከንባታ፣ ወላይታና ሲዳማ ዞኖች ለረጅም ዘመናት እንሰትን በማምረት የሚጠቀሱ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በእንሰት አምራችነቱ የሚታወቀው የሃዲያ ህዝብ ኑሮ ለረጅም ዓመታት በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሰረተ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ነገር ግን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በተከሰተው በሽታ የእንስሳት ሃብቱ በማለቃቸውና የሸዋ ወራሪ ሃይል አካባቢው መቆጣጣሩን ተከትሎ የግብርና ምርቶችን በግብር መልክ እንዲያቀርብ በመገደዱ ምክንያት የእርሻ ስራ እንዲላመድ በር መክፈቱን አቶ አለባቸው ኬዕምሶ እና አቶ ሳሙኤል ሃንዳሞ የተባሉ የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በአካባቢው ከታወቁ የእርሻ ምርቶች መካካል የእንሰት ተክል በዋናነት ይጠቀሳል። እንሰት በአከባቢው ቀድሞ የታዋወቀው ለዞኑ አጎራባች በሆኑት የጉራጌና የከምባታ ዞኖች መሆኑ ይነገራል። በተለይም ከ1900 እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ የአከባቢው ህብረተሰብ የተክሉ ጠቃሜታዎች በስፋት በመረዳቱ በከፍተኛ ደረጃ ያመርተው እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። ዘውዳዊ አገዛዙን መገርሰሱን ተከትሎ የመንግስትነት ስልጣን የተቆናጠጠው ወታደራዊው የደርግ ስርዓት በ1974 ዓ.ም የአከባቢውን ህዝብ በሰፈራና በመንደር ማሰባሰብ ሰበብ ህዝቡ ተረጋግቶ ይኖርበት ከነበረው አከባቢ ያለፈላጎቱ ከቀየው እንዲፈናቀልና መንግስት የሚፈልጋቸውን የስንዴና የበቆሎ ምርቶች ብቻ እንዲያመርት በመገደዱ ምክንያት የእንሰት ምርት ስራ ተቀዛቅዞ ነበር።